ለውጡን መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ አደራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ለውጡን መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ አደራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 ባለፈው አንድ ዓመት በመደመር ሀሳብ የመጣውን አገራዊ ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ አደራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ የተደረገበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 'ከመጋቢት እስከ መጋቢት' የተባለ መርሃ-ግብር ትናንት ምሽት በሚሌኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ እንደተናገሩት፤ "በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንድና በፈጣሪ እርዳታ የመጣውን ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል" ይገባል።
"በወቅቱ የነበረው ጨለማ ተገፎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የደስታ ብርሃን ያየበት በመሆኑ ለውጡ እንዴት እንደመጣ መዘንጋት የለበትም" ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጡ የጥቂቶች ብቻ እንዳልሆነም አብራርተዋል።
"ለውጡ እንደ ውኃ ፈሳሽ፣ እንደ እንግዳ ደራሽ የመጣ አልነበረም፤ ብዙዎች የሞቱለት፣ የተገረፉለት፣ የታሰሩለት፣ የተሰደዱለት፣ ያለቀሱለት፣ የጸለዩለት የሁላችን ድምር እንጂ የጥቂት ግለሰቦች አልነበረም። ይህ በብዙዎች ዋጋ የመጣን ለውጥ በተባበረ ክንድ በመደመር ሀሳብ መጠበቅና ማስቀጠል ከመላው የኢትዮጵያውያን ህዝቦች የሚጠበቅ አደራ ይሆናል"።
የአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት "ባልተሟሸ ጀበና እንደተጣደ ቡና በረባ ባልረባ ጉዳይ ቱግ ቱግ የማለት ባህርይ አለው" ያሉት ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች "የህዝቡ ዝምታ እንደ ሬሳ፣ ቁጣው እንደ አንበሳ መሆኑን ማሰብ ይኖርብናል" ሲሉ አሳስበዋል።
ባለፈው ዓመት የተጀመረውን ለውጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፀጋ እንደተቀበለውና የተገኙ ድሎችን በአዳዲስ ድሎች ለማስቀጠል መንግስት ዕቅድ እንዳለው አረጋግጠዋል።
"ተርቦ የከረመ ሰው መጀመሪያ ያገኘውን ዳቦ በተለየ ፍቅርና አድናቆት እንደሚጎርሰው ሁሉ ለውጡን በአንድ ልብ ከጎረስን በኋላ ረሀባችንን አስታግሰን የዳቦን ከለር ጣዕምና ማጣቀሻውን እንደሚመርጥ ረሀብተኛ አሁን ግራና ቀኝ ማማተራችንና መፈለጋችን ሰዋዊ ባህርይ ነውና እንደ እንግዳ ባህርይ የማናየውን ነገር ግን የጠገበ ሰውን ደረቅ ዳቦ ብቻ ሳይሆን ጣፋጭ ከጎኑ ማስቀመጥ ግዴታችን መሆኑን ተገንዝበን ለህዝባችን የባለፈውን ድል በመናገር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ድል በማስመዝገብ ኢትዮጵያውያንን ዳግም እንደምናኮራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ"።
ለውጡ እንደ ጤዛ ታይተው የሚጠፉ ችግር ፈጣሪዎችን እንደሚያመጣ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝናብ ተፈርቶ ክረምትን ማስቀረት እንደማይቻል ሁሉ ለውጡ ባልተለወጠ ተቋምና ማህበረሰብ በመሆኑ መንገራገጭ ያጋጥማል ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ንግግር፤ በመደመር ፍልስፍና የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና በሚጫወተው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የዜጎች የፍትህ እጦት ስቃይን ለማስቀረት በፍትህ ስርዓቱ ላይ የለውጥ እርምጃ ተወስዷል።
"ለውጥ የሚያስቸግረው ባልታደሰ ተቋም ሲጀመር ነው፤ ለውጡን ስንጀምር የሚያሻግር የመደመር ፍልስፍና ብናበስርም ባልተለወጠ ባህልና ባልተለወጠ ተቋም ነውና መንገራገጭ አይቀሬ ነው፤ ለዚህም ሲባል ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን አይተኬ ሚና የሚጫወተው የምርጫ ቦርድ ስናደራጅ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ታስራ ለፍትህ በጀግንነትና ለመላው ኢትዮጵያውያን አርአያ የሆነችውን በርቱካን ሚደቅሳን ያመጣነው። የፍትህ እጦት ኢትዮጵያውያንን እንዳንገሸገሸ ስለምናውቅ እናት፣ እህት ሚስት ሆና ፍትህ የሚሹትን በመለየት በማስተማር ለማንም ዝቅ ሳትል በህግና በህግ ብቻ ፍትህ ለኢትዮጵያ እንድታመጣ ወይዘሮ መአዛን ለፍትህ ስርዓት እንዳመጣን አይዘነጋም"።
በአሁኑ ወቅት በአማራና በትግራይ፣ በሶማሌና በአፋር፣ በጌዲዮና በጉጂ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር ሰይፍ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር ሰይፉን በመምዘዝ እንደ ጥንቱ ታላቅ የሚያደርገውን አገራዊ አንድነት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያውያን ሰይፍ ያስፈልገናል፤ በአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል ሰይፍ ያስፈልገናል፤ ያ የሚያስፈልገን ሰይፍ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር ነው። በሶማሌና በአፋር ህዝቦች መካከል እንዲሁ ሰይፍ ያስፈልገናል፤ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር በጎዲዮና በጉጂ ህዝቦች መካከል ሰይፍ ያስፈልገናል፤ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የለመድነውን አንገት የሚቀላውን ሰይፍ ሳይሆን የሰላሙን፣ የይቅርታውንና የፍቅሩን ሰይፍ በመምዘዝ ኢትዮጵያ እንደ ጥንቱ ታላቅ የማድረግ ፕሮጀክት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ እንጂ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የማይጠበቅ መሆኑን እንዲሁ ልገልጸላችሁ እፈልጋለሁ። "
በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ፣ በግብርና ዘርፍ የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶችን በመጠቀም በገጠር የሚኖሩ ወጣቶችን ወደ አምራችነት መቀየር፣ ከመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ታላቁ ቤተ መንግስትን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ አዲስ አበባን የቱሪዝም መናኸሪያ ማድረግ እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲካሄድ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ገልጸዋል።