ቀጥታ፡

13ኛው "የአውሮፓ ቀን" የህጻናት ሩጫ ውድድር ሚያዚያ 27 ይካሄዳል

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ለ13ኛ  ጊዜ "የአውሮፓ ቀን" በማስመልከት በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 2 ሺህ 750 ህጻናት የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ይካሄዳል።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽህፈት ቤትና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሩን አስመልክቶ በህብረቱ ጽህፈት ቤት በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አምባሳደር ጆን ቦርግስታም ''በውድድሩ ከሚሳተፉ ህጻናት የነገዎቹ የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች የሚገኙበት መሆኑን አልጠራጠርም'' ብለዋል።

ውድድሩ ህጻናት ጤናቸው እንዲጠበቅና በስነ ልቦና ያላቸውን ዝግጁነት እንዲያድግ ከማድረግ አንጻር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

አትሌቲክስ ባለው ተቀባይነትና ስኬት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትልቅ ምልክት እንደሚታይና ስፖርቱ በሁሉም ደረጃ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚነካ መሆኑን አውስተዋል።

በዚህ ረገድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ በሆኑ አትሌቶቿ በምትታወቀው ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የህጻናት ሩጫ ውድድርን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በማካሄዱ ትልቅ ክብር እንደሚሰማውም ገልጸዋል።

ውድድሩ የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ ካላቸው ስትራቴጂካዊ ትስስር ዋነኛ ከሆኑት መካከል ወጣቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ የልማትና የኢኮኖሚ ተግባራት አካል ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንዳብራሩት፤ ከአምስት ዓመት በታች የእድሜ ክልል ያሉ ታዳጊ ህጻናት 300 ሜትር፣ ከስምንት ዓመት በታች 800 ሜትር፣ ከአስራ አንድ ዓመት በታች 1 ሺህ ሜትርና ከ14 ዓመት በታች 1 ሺህ 400 ሜትር ይሮጣሉ።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ታዳጊ ህጻናት የሚያሳትፉ ውድድሮች እንደሚያዘጋጅ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ህጻናት ብቻ የሚካፈሉበት ውድድር እንዳለ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በተካሄዱት የአውሮፓ ቀን "የህጻናት ሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፉ ታዳጊዎችን ከስር በመከታተል የመመልመልና ብቁ የማድረግ ስራ መሰራቱን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ፤

"የሁለቱ አካላት ተግባር የውድድር እድሉን መፍጠር እንደሆነና የመመልመልና ለወደፊት ተተኪ አትሌቶችን የማፍራት ስራ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተግባር ነው" ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ህብረት ልዑክ ሃላፊ አምባሳደር ራኒየሪ ሳባቱቺ በበኩላቸው ከህጻናት የሩጫ ውድድሩ በተጨማሪ የአውሮፓ ቀን በሙዚቃ ፌስቲቫልና የማነቃቂያ ንግግር ይዘት ባለው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተከብሮ እንደሚውልም ገልጸዋል።

ፕሮግራሞቹ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ እንዲሁም በአጠቃላይ ከአፍሪካ አህጉር ጋር በባህል መስክ ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚረዳም አክለዋል።

በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን ለአሁኑ የአውሮፓ ህብረት መፈጠር መሰረት የሆነውን እ.አ.አ በ1950 የተፈረመው የጀርመንና ፈረንሳይ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ውህደት ስምምነት ታስቦ ይውላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም