ያልተበረዘ ባህልን ለትውልድ ለማውረስ እየሰራ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ያልተበረዘ ባህልን ለትውልድ ለማውረስ እየሰራ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ
ደሴ መጋቢት 25/2011 በመጤ ባህል ያልተበረዘ ባህል ለትውልድ ለማውረስ እየተሰራ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስታወቁ።
ሦስተኛው አገር አቀፍ የባህል ዐውደ ጥናት"ቋንቋና ባህል ለአገር ግንባታ!" በሚል መሪ ቃል በወሎ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን እንደገለጹት ዩንቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመጤ ባህል ያልተበረዘ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ባህል ለትውልዱ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን መቻቻል፣የመከባበር፣ የመረዳዳት፣ የፍቅርና የአንድነት ባህል እንዲያንሰራሩ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ በምዕራባውያን አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አነጋገር፣ የአኗኗርና በሌሎችም መጤ ባህል ተጠምዶ ኢትዮጵያዊ ባህሉን እየረሳ ከመጣበት ሁኔታ ማውጣት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ትውልዱ ባህሉንና ቋንቋውን እንዲያውቅ በጥናት የታገዘ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ መሆኑን ዶክተር አባተ ተናግረዋል።
በዚህም የግዕዝ ቋንቋ ማስተማር ጀምሯል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ፣ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው እንደተናገሩት "የተጠናወተን የቋንቋና ባህል ወረርሽኝ ሁሉም በጋራ በመከላከል ኢትዮጵያዊ የመቻቻልና የአንድነት ባህላችንን ማጎልበት ያስፈልጋል።"
ኢትዮጵያውያንን በማይመጥኑ መጤ ባህል ታሪክን ማስወቀስ ስልጣኔ አለመሆኑን ያስረዱት ምሑሩ፣ ወግና ባህሉን ጠብቆ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ኋላቀርነትና ድህነትን ማሸነፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"በየቤተ ክርስቲያኑና መስጊዶች ተጠግተን ብንማር የኪነ-ጥበብና የቋንቋ ጉድለት እንደሌለብን እንረዳለን" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የባህርዳር ጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንት ሊቀህሩያን በላይ መኮንን ሥርዓተ ትምህርቱ ለባህል የሚሰጠው ሽፋን አናሳ በመሆኑ ኢትዮጵያን የማይወክል በየአካባቢዎቹ ስሜት በመንጸባረቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
"የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ታላላቆችን፣እንግዳ የማያከብር፣ የሚገላምጥ፣ ቤት የሚዘጋ፣ ዋሾ፣ እምነት አጉዳይ ትውልድ በመፈጠሩ ሁላችንም ተወቃሽ ነን"ሲሉም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ አዝመራው በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ ጥናቶችን በመጠቀም ባህልን ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከነዚህም በትምህርት ቤቶች የባህል ክበባት በማቋቋም ተማሪዎች ባህልና ወጎችን እንዲረዱ ማድረግ ይገኝበታል።
በዐውደ ጥናቱ 24 ጥናታዊ ጹሑፎች እየቀረቡበት ሲሆን፣ከ15 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ከ150 በላይ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ነው፡፡