ቀጥታ፡

እንደ ሃገር የመጣውን ለውጥ ክፍተቶችን በማስተካከል ማስቀጠል እንደሚገባ ፖለቲከኞች አመለከቱ

ባህርዳር መጋቢት 25/2011 እንደ ሃገር የመጣውን ለውጥ በመደገፍ ያሉበትን ክፍተቶች   አሰተካክሎ  ማስቀጠል እንደሚገባ ፖለቲከኞች አመለከቱ፡፡

በሀገሪቱ ያለፈውን ዓመት የለውጥ ጉዞ  ላይ የሚመክር መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ  የመነሻ ጽሑፍ ካቀረቡ ፖለቲከኞች መካከል አቶ ልደቱ አያሌው እንዳመለከቱት ለውጡ ግልጸኝነት የሚጎድለው ቢሆንም ሃገሪቱን ወደ ከፋ መንገድ ሊወስዳት ከነበረው ማጥ ያወጣ ነው፡፡

የለውጡ አመራሮች ሂደቱን ግልጽ ማድረግ የሚጠበቅባቸው እንዳለ ሆኖ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጡን ለማስቀጠል መረባረብ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

ከኢህአዴግ  በወጡ አመራሮች የመጣው  ለውጡ ብዙም ዋጋ ሳያስከፍል  ቢሆንም  ቀጣይ ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ የለውጡ አመራሮች በውሳኔ ሰጪነትና የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ቁርጠኛ አቋም ሊያሳዩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ልደቱ ገለጻ   አሁን ያለው ለውጥ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን ህዝቡ በቅሬታ ሲያነሳቸው የነበሩ ያሻሻለ ሰራ ነው፡፡

ሆኖም ሃገሪቱን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የከተተው የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ-መንግስት እስካልተሻሻለ ድረስ ለውጡ የመቀልበስ  ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ህገ-መንግስቱ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ  የሚሻሻልበት መንገድ በፍጥነት ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላኛው የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢ ዶክተር አረጋዊ በረሔ በበኩላቸው ለውጡ በሃገሪቱ አሳዳጅና ተሳዳጅ ህዝብ ሲኖርባት ከነበረበት የፖለቲካ ማጥ እንዲወጣ ያስቻለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ለውጡ አሁንም የሚስተካከሉ ችግሮች ቢኖሩበትም   ከመደገፍ ውጭ ለለውጡ መቀልበስ ምክንያት የሚሆኑ ሃሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ ይገባል " ብለዋል።

የለውጡን ግልጸኝነት በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ  ጥያቄ የተነሳበት ቢሆንም  በአንድ ዓመት ሊታሰብ በማይቻል መልኩ ከነችግሮቹም ቢሆን ሃገሪቱን ከከፋ ችግር የመለሰ መሆኑን ዶክተር አረጋዊ ገልጸዋል፡፡

ለውጡን ከመንቀፍ ይልቅ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ለውጡን የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን በመሰንዘር የራሳቸውን የተሻለ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ወጣቱ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ለውጥ ለመቀልበስ ሳይሆን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንዳሉት  ከዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታ የጨቋኝና የተጨቋኝ ፖሊሲ በመሆኑ ህዝቡ አግላይና ተገላይ ሆኖ ቆይቷል።

ይሔንን የአንድ ዓመት ለውጥ ምንም እንዳይደለ መኮነን ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የሚስማማበት የግልጸኝነት ጥያቄ የለውጡ አመራር እያሰበበት በመሆኑ  ለውጡን የሚጎለብትባቸው  ሃሳቦችን መሰንዘር ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም