የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ዛሬ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ዛሬ ይጫወታል
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ነው ዛሬ ከዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው።
ብሔራዊ ቡድኑ ለማጣሪያ ጨዋታው ከመጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ልምምድ ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን ለዚህም ጨዋታ የመጨረሻ 25 ተጫዋቾች ተለይተዋል።
የቡድኑ አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ መሆናቸውንና ቡድኑ ለሚያደርገው ጨዋታም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጻለች።
በአጠቃላይ 28 የቡድን አባላትን ይዞ ትናንት ማለዳ አዲስ አበባ የገባው የዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ማምሻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሊያደርግ የነበረ ቢሆንም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ልምምዱን ሳያደርግ ቀርቷል።
ይህም ለኢትዮጵያ ብሔረዊ ቡድን መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።
የመልስ ጨዋታቸውን ከሦስት ቀናት በኋላ በዩጋንዳ ካምፓላ የሚያደርጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ድል ከቀናው በቀጣይ ከካሜሮን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚገናኝ ነው የሚሆነው።
የዛሬውን የኢትዮጵያ እና የዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን የመጀመርያ የማጣሪያ ጨዋታ የሚዳኙት አራቱም ዳኞች ግብጻዊያን ይሆናሉ።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በኦሎምፒክ ጨዋታዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተለይ በአትሌቲክሱ ብዙ ታሪክ ብታስመዘግብም በእግር ኳስ ግን እስከ ዛሬ ተሳትፋ አታውቅም።