ቀጥታ፡

በዴንማርክ የተገኘው አኩሪ ውጤት በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ መድገም ይገባል''- ዶክተር ሂሩት ካሳው

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2011 በዴንማርክ የተገኘውን አኩሪ ውጤት በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ መድገም ይገባል ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳሰቡ።

ባለፈው ቅዳሜ በዴንማርክ  አርሁስ በተካሄደው 43ኛው  የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር በ5 ወርቅ፣ በ3 ብርና በ3 የነሐስ ሜዳሊያ ከዓለም አንደኛ ለወጣው የኢትዮጵያ ልዑክ የአቀባበል ስነ ስርዓትና ሽልማት ተበርከቶለታል።

በውድድሩ የተካፈለው የልዑካን ቡድን ዛሬ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ከባሀልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገንዘብ  ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዴንማርክ የተገኘው ድል ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ያስጠራ ነው ብለዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ አትሌቶች በቡድን ወይም በትብብር ሳይሆን  በግል ውድድር ላይ ማተኮር ይታይባቸው እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ውድድር ግን  እንደ አረንጓዴው ጎርፍ  ከግል ይልቅ በጋራ በመስራት አኩሪ ውጤት በማምጣት ኢትዮጵያን በማኩራታችሁ ልትኮሩ ይገባችኋል ብለዋል።።

በቀጣይም በኳታር የዓለም ሻምፒዮና፣ በጃፓን የኦሎምፒክ ውድድርና በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ይህን ውጤት መድገም ይገባል ሲሉም ነው ያሳሰቡት።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም እስካሁን ሲያደርግ ከነበረው በላይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ  እንደሆነ በማከል።

የኢትጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚብሄር ገብረማሪያም በበኩሉ "ውጤቱ ተኩራርተን የምንቀመጥበት ሳይሆን በቀጣይ ኢትዮጵያ ላሉባት ውድድሮች የሞራል ስንቅ ሊሆነን ይገባል" ብሏል።

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች 30 ሺህ ብር ፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ 20 ሺህ ብር፣ የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ ደግሞ የ10 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላገኙ 6 ሺህ ብርና በውድድሩ ለተሳተፉ አትሌቶች ደግሞ 3 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከአትሌቶች በተጨማሪ ለአሰልጣኞች፣ ለህክምና ባለሙያዎችና ለሌሎች የቡድኑ አባላትም ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን ፌዴሬሽኑ ለሽልማት ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ነው የተገለጸው።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ወርቅ ላመጡ 15 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ  ላመጡ 10 ሺህና ነሐስ  ላመጡ 5 ሺህ ብር እንዲሁም ለአሰልጣኞችና ለሌሎች የቡድኑ አባላትም ሽልማት ያበረከተ ሲሆን  በድምሩ ከ300 ሺህ ብር በላይ ለሽልማት ወጪ አድርጓል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ለሀገራቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች የ20 ሺህ ብር፣ የ15 ሺህና የ10 ሺህ ብር ሽልማት እንደየቅደም ተከተላቸው የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

በዚህ ሻምፒዮና 28 አትሌቶች ኢትጵያን ወክለው የተካፈሉ ሲሆን በውድድሩ አምስቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች አንዱ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር በአትሌት ሚልኬሳ መንገሻ፣  አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብልና ቀሪዎቹ የወርቅ ሜዳሊያዎች ደግሞ በአዋቂ ሴትና በሁለቱም ጾታ ወጣት ቡድን የተገኙ ናቸው።

ሶስቱ የብር ሜዳሊያዎች ደግሞ በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር በአትሌት ደራ ዲዳ ፣በወጣት ሴቶች በ6 ኪሎ ሜትር በአትሌት አለሚቱ ታሪኩና በወጣት ወንዶች ደግሞ በአትሌት ታደሰ ወርቁ የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

በአዋቂ ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ በወጣት ሴቶች ፅጌ ገብረሰላማና በአዋቂ ወንዶች የቡድን ውጤት ሶስቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል።

---END---

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም