ቀጥታ፡

ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አማካኝነት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እንዲሰራ ምክር ቤቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ  መጋቢት 24/2011 በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አማካኝነት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመፍታት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በትኩረት እንዲሰራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ8 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

ምክር ቤቱ ስራና ሰራተኛ ለማገናኘት ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች በህጋዊ መንገድ መስራታቸውን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር ማጠናከር እንዳለበትም አሳስቧል።

በተለይ የአገር ውስጥ ኤጀንሲዎች ከሚያስቀጥሯቸው ግለሰቦች ከሚከፈለው ደሞዝ በላይ ኤጀንሲው ከተቀጣሪዎቹ  የሚወስደው እንደሚበልጥ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ከምክር ቤቱ አባላት ተጠቅሷል።

በአገር ውስጥ የሥራና ሰራተኛ ማገናኘት ፍቃድ ተሰጥቷቸው ጥበቃንና ፅዳትን ጨምሮ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ሰራተኞችን የሚያስቀጥሩ ኤጀንሲዎችን ለአብነት  አነስተዋል።

በእነዚህ ኤጀንሲዎች አማካኝነት ሥራ ተገኝቶላቸው በተለያዩ ድርጅቶች የሚሰሩ ሰራተኞች አብዛኛው ደሞዝና ጥቅማጥቅም በኤጀንሲዎቹ ስለሚወሰድ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፁ የሚሰማ መሆኑም በምክር ቤቱ ተነስቷል።

በዚህም ሰራተኞች የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ በመግለፅ ጉዳዩ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አባላቱ አሳሰበዋል። 

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሰጡት ምላሽ እንዳሉ ይህንን ችግር ለመቀነስ የአገር ውስጥ የግል ስራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስራ ስምሪት አገልግሎት አሰጣጥ የሚወስን ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው።

ከዚህም ሌላ መስሪያ ቤታቸው ባለፉት ስምንት ወራት ባካሄደው ቁጥጥር ከሀግ ውጭ ሲሰሩ የተገኙ ከ150 በላይ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ የፈቃድ እገዳን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰደም ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት በአዲሰ አበባ ብቻ በተካሄደው ቁጥጥር ህግን በመተላለፍ ከስራ ፈላጊዎች ገንዘብ ሲቀበሉ በተገኙ 113 ኤጀንሲዎች ላይ የሥራ ፈቃድ እገዳ መደረጉን ሚኒስትሯ አስታወቀዋል።

በተጨማሪም 22 ኤጀንሲዎች ፍቃድ ሲሰረዝ 'በከፍተኛ ደሞዝ እናስቀጥራለን' በማለት ከስራ ፈላጊዎች ላይ ከ200 እስከ 300 ብር የተቀበሉ 20 ኤጀንሲዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለሚመለከተው አካል መተላለፉንም ጠቅሰዋል።

የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ከፀደቀ የቆየ ቢሆንም  እስካሁን ወደ ስራ አለመግባቱ አግባብ አለመሆኑን በምክር ቤቱ አባላት በስፋት የተነሳ ጉዳይ ነበር።

የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ ሰራተኞችን ከሚቀበሉ አገራት ጋር ስምምነቶችን ማድረግ፣ ስልጠናዎችንና  ለኤጀንሲዎች ፈቃድ መስጠትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ተንከባካቢ ያጡ አረጋዊያንንና ህጻናትን ህይወት ለመታደግና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማቋቋም ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚያከናወነውን ተግባር ማጠናከር |እንዳለብም ተወሰቷል።

ማህበራዊ  ችግሮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳተፎ በማጠናከር ዘላቂ የሆነ ኃብት ለማሰባሰበ የሚያስችል ፈንድ ይቋቋማል ተብሏል።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት "የማህበራዊ ዋስትና ፈንድ" በሚል የሚቋቋመውን ተቋም እውን ለማድረግ አዋጅ ተረቆ ለሚኒስትሮ ምክር ቤት ቀርቧል። 

አዋጁ በፍጥነት ታይቶና በሚመለከታቸው አካላት ፀድቆ ወደተግባር መግባት እንዳለበትም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም