ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የሚካሄደውን የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ለማስተናገድ ጥያቄ አቀረበች

አዲስ አበባ  መጋቢት 24/2011 ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የሚካሄደውን የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ለማስተናገድ ለዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጥያቄ አቀረበች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ ''ውድድሩን እንደ አደጉት ሀገራት በታላቅ ድምቀት ማስተናገድ ባንችልም የተቻለንን ሁሉ አድርገን ውድድሩን ለማዘጋጀት ጥያቄውን አቅርበናል'' ብላለች።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ውድድር ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ትታወቃለች።

ሀገሪቷ እያሳየች ያለውን ለውጥ ተከትሎ ከፍተኛ ውጤት የምታስመዘግብበትን ውድድር የማስተናገድ አቅሙም አላት ብላለች።

ይህን ውድድር ማዘጋጀት ማለት በቀጣይ ሌሎች ትላልቅ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ያለንን አቅም የምንፈትሽበትና ራሳችንን የምናይበት ይሆናልም ብላለች።

የጥያቄው ምላሽ የሚታወቅበት ጊዜ ገና ቢሆንም የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ኢትዮጵያ ይህን ውድድር ለማስተናገድ ጥያቄ በማቅረቧ ደስተኛ መሆኑ ነው የተነገረው።

ከ1965ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘውን የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ዩጋንዳ አዘጋጅተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም