ቀጥታ፡

የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማህበር የገንዘብና የተሽከርካሪ እርዳታ አገኘ

መቀሌ መጋቢት 24/2011 የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማህበር    7 ሚሊዮን ብርና አንድ ተሽከሪካሪ ዛሬ በእርዳታ አገኘ፡፡

እርዳታውን ያደረጉት አምስት የቻይና ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ትብብር ሲሆን  መቀሌ ከተማ  በመገኘትም ለማህበሩ አስረክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጨርቆስ ወልደማሪያም ናቸው።

ከቻይና ኩባንያዎችና በኤምባሲው በኩል የተደረገው እርዳታ ከሁሉም በላይ የአካል ጉዳተኞችን ክብርና ፍቅር ለመግለጽ መሆኑን በኢትዮጰያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ አማካሪ ኮሚሽነር ማድያም ሊ ዩ ተናግረዋል።

ሰላም፣ዴሞክራሲና ልማትን ለማረጋገጥ በተካሄደው የትጥቅ ትግል አካላቸው ላጡ ታጋዮች ኩባንያዎቹና ኤምባሲው ባደረጉት ድጋፍ ልዩ ክብር እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ የቻይና መንግስት ከኢትዮጰያ ጋር የነበረውን የረጅም  ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት  አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የቻይናና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለነጻነታቸው መከበር የከፈሉት መስዋእትነት ተመሳሳይነት አለው" ያሉት ኮሚሽነሯ፣ የሁለቱም ህዝቦች ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የቻይና ኩባንያዎች ልዕኳን ቡድን አባላትን በመወከል  ሚስተር ዋን ኪንግ ዣንግ እንደተናገሩት ድጋፉ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ለዘመናት የቆየውን መልካም ግንኙነት  ለማጠናከር ያግዛል።

ድጋፉ የትግራይ የጦር አካል ጉዳተኛ ማህበር እንቅስቃሴን ለማጠናከር  እንደሚረዳውም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በእርዳታ ርክክቡ ስነስርዓት ወቅት ተገኝተው "የድጋፉ ትርጉም ከሁሉም በላይ ለታጋዮች ያለንን ጥልቅ ፍቅርና ልዩ ክብር ማሳያ ነው" ብለዋል።

"ድጋፉ በቻይና እና  ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የቆየ  ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በተለይም ለትግራይ ህዝብ ክብር ሲባል የተደረገ  በመሆኑ የክልሉ መንግስትና ህዝብ የተለየ ስፍራ  አለው "ብለዋል።

የትግራይ ክልላዊ መንግስት የቻይና ባለሃብቶች በክልሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ እያሳዩ ላለው  ከፍተኛ ፍላጎት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን ድጋፍ ላደረጉ ኩባንያዎችና ኤምባሲው ምስጋና አቀርበዋል፡፡

ድጋፉ የደርግ ሰርዓትን ለመጣል ተካሄዶ በነበረው የትጥቅ ትግል ወቅት የጦር ጉዳተኛ የሆኑ ታጋዮች የሚውል መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም