የያዮ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የያዮ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ተሰጠ
መቱ ግንቦት 24/2010 በኢሉአባቦር ዞን ያዮ ወረዳ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት በማህበር ለተደራጁ የአካባቢው ወጣቶች ተሰጠ፡፡ ፕሮጀክቱን ለወጣቶቹ ለማስተላለፍ ትናንት በተዘጋጀው ስነስርዓት የኦሮሚያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ አወሉአብዲ እንዳሉት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ "የያዮ የድንጋይ ከሰል ፕሮጄክትን በአካባቢው በማህበር ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች ተላልፎ መሰጠቱም የዚሁ ማሳያ ነው "ብለዋል፡፡ በቢሮው የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ጎንፋ ባልቻ በበኩላቸው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ስፍራው ከዚህ ቀደም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር ሆኖ ኮርፖሬሽኑ በማምረት ለገበያ ያቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የማዕድኑን አመራረትና አጠቃቀም ለመገምገም ኮሚቴ ተቋቁሞ አሰራሩን ከተጣራ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ከኮርፖሬሽኑ የተላለፈላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ "ከዚህ ቀደም በፕሮጄክቱ በቀን ሰራተኛነት ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ጨምሮ 171 ወጣቶች በሁለት ማህበራት ተደራጅተው ወደ ማዕድን ማምረቱ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል" ያሉት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ ናቸው፡፡ የአይካ አዲስ ቴክስታይልና ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ ጫላ በበኩላቸው ድርጅታቸው በቀን 70 ቶን የድንጋይ ከሰል እንደሚፈልግና ለወጣቶቹ አስፈላጊው የመሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ምርቱን እንደሚረከቡ ተናግረዋል፡፡ ማዕድኑን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ራሳቸውን ለመለወጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ የማህበራቱ አባል ወጣቶች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡