ቀጥታ፡

ኢስታንቡል-የአየር መንገዱ 120ኛ መዳረሻ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2011የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቱርክ  ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ ጀመረ።

አየር መንገዱ በረራውን መጀመሩን አስመልክቶ ያዘጋጀው ፕሮግራም ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል።

ትናንት ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ5 ደቂቃ መንገደኞችን ይዞ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተነሳው አውሮፕላን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ደርሷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል ዑመር፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስና የአየር መንገዱ የስራ ሃላፊዎች በበረራው ወደ ኢስታንቡል አቅንተዋል።

አየር መንገዱ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ የሚያደርገው በሳምንት ሶስት ቀናት ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አየር መንገዱ ወደ ኢንስታንቡል በረራ መጀመሩ የሁለቱ አገራትን የቆየ ባህል፤ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ግንኙነት ያጠናክራል።

አየር መንገዱ በአፍሪካ ካለው ተደራሽነት አንጻርና ለደንበኞች ከሚሰጠው ቀልጣፋ አገልግሎት አኳያ ዋና የቀጥታ በረራው ስለሚኖረው ፋይዳ ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደዚህ ያስረዳሉ።

"በኢትዮጵያና በቱርክ ብቻ ሳይሆን ይሄ በረራ የአፍሪካ አገሮች ያገናኛል። ምክንያቱም ከስልሳ በላይ የሚሆኑ ከተሞች ውስጥ እንበራለን አፍሪካ ውስጥ እና በረራዎቹን ዲዛይን ያደረግናቸው ጠዋት አፍሪካ ሄደው በሙሉ ከአፍሪካ ስለሚመለሱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ በሙሉ የአፍሪካ በረራዎች መንገዶኞች ይዘው ይመጣሉ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ደግሞ ወደ ኢስታንቡል ይበራሉ። ሶ፤ በአጭር ጊዜ ቅብብሎሹ ለመንገደኛ ምቹ በሆነና ብዙ መንገደኛ ጊዜ ሳያጠፋ በአጭር ጊዜ ከማንኛውም የአፍሪካ ከተማ ተነስቶ ኢስታንቡል የሚገባበት ሁኔታ ነው የፈጠርነው።" ብለዋል፡፡

አውሮፕላኑ ከኢስታንቡል ወደ አዲስ አበባ በረራ በሚያደርግበት ወቅትም ተመሳሳይ አገልግሎት ለተሳፋሪዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ወደ ኢስታንቡል የተጀመረው በረራ አፍሪካን ከአውሮፓ በማገናኘት ለአየር መንገዱ ደንበኞች ሌላ የግንኙነት አማራጭ ይሆናልም ብለዋል።

በረራው በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቱርክ አየር መንገድ ባላቸው የመንገደኞች የመለዋወጥ ስምምነት ከኢስታንቡል ወደ ሌሎች ቦታዎች የሚቀጥሉ መንገደኞች ከቱርክ አየር መንገድ ጋር በመተባበር እንደሚስተናገዱበትም ነው አቶ ተወልደ ያስረዱት።

በቀጣይ ጊዜም ወደ ኢስታንቡል በሳምንት ሶስት ጊዜ የሚደረገው በረራ ወደ ሰባት ቀን ለማሳደግ የሚያስችል ስራም እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቱርክ አየር መንገድ የአየር መንገዶች ማህበር የሆነው የስታር አሊያንስ አባል እንደሆኑና የተጀመረውም በረራ በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል።

አየር መንገዱ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ሂውስተን ቴክሳስና ፓሪስ በተጨማሪ በሌላኛዋ የፈረንሳይ ከተማ ማርሴይ በረራ ለመጀመር እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ሚስ ያፕራክ አልፕ በበኩላቸው የቀጥታ በረራ መጀመር በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠክረው ገልጸዋል።

የቀጥታ በረራው በሁለቱ አገራት በሚካሄዱ የንግድ ትርኢትና ባዛሮች የሚሳተፉ የአገራቱ ዜጎች ቁጥር ለመጨመርም ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ቱርክ በአፍሪካ ካሉ አገራት ኢትዮጵያ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አጋሯ እንደሆነችና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የቱርክ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በአምባሳደርነት ቆይታቸውም የሁለቱን አገራት ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

ወደ ኢስታንቡል የቀጥታ በረራ የጀመረው አየር መንገዱ በአጠቃላይ በአውሮፓ ያለውን መዳረሻ ወደ 19 ከፍ ያደረገው ሲሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለውን የበረራ መዳረሻዎችንም ወደ 120 ከፍ እንዲል አድርጎታል።

በተጨማሪም አየር መንገዱ ኢስታንቡልን ጨምሮ ወደ አውሮፓ አገሮችም በሳምንት 57 ጊዜ የሚበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም