ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጃፓን የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ቀረበላቸው

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጃፓን የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ቀረበላቸው።

ዶክተር አብይ ግብዣው የቀረበላቸው አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን የሹመት ደብዳቤአቸውን ለጃፓን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ታኬኦ አኪባ ትናንት ባቀረቡበት ወቅት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ታኬኦ አኪባ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥና በኢትዮጵያ አዲስ አመራር መምጣቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለይ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ሰላማዊ በማድረግ በኩል የወሰዷቸውን እርምጃዎችን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለማስቀጠል ፍላጎት ያላት መሆኑን በመግለጽ፣ ለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ በነሐሴ 2019  7ኛው የጃፓን-አፍሪካ የልማት ፎረም (የቲካድ 7) የመሪዎች ስብሰባ በጃፓን ዮኮሃማ ከተማ እንደሚካሄድ በማስታወስ ኢትዮጵያ በመድረኩ ላይ በመሪ ደረጃ ተሳትፎ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከቲካድ 7 ስብሰባ ቀደም ብለው በጃፓን የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉም ጋብዘዋል።

አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡበት ቀን በጃፓን የአዲስ ንጉስ ንግስና የሚረከቡ መሆኑን ተከትሎ የሚመጣው አዲስ ዘመን የሚጠራበት ስም ይፋ በተደረገበት ቀን መሆኑ ታሪካዊ እንደሆነም ገልጸዋል።

መጪው ጊዜም የጃፓንና የኢትዮጵያ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚጎናጸፍበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በጃፓን ቆይታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲዳብር የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም አምባሳደር ካሳ ተናግረዋል።

አምባሳደር ካሳ በጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ሺጌሩ ኡሺዮና ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር በመሆን ካገለገሉ ሁለት ከፍተኛ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1930 ሲሆን እ.አ.አ በ1958 አገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል።

ሁለቱም አገራት በልማቱ መስክ ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሲሆን የጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት(ጃይካ) በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

አገራቱ በንግዱ ዘርፍ መልካም ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ጃፓን ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመሞችን ስትልክ መኪናዎች፣ የማሽነሪ እቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስና የህክምና እቃዎች እንዲሁም የብረታ ብረት ምርቶችን ደግሞ ታስገባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም