ምክር ቤቱ ከቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንደሚገባው አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ከቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንደሚገባው አሳሰበ
አዲስ አበባ መጋቢት 23/2011 የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የሚያስገነባውን የመንገድ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገድብ ማጠናቀቅ እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ በመንግስት ወጪና በብድር ከሚሰሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ ፕሮጀክት ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል።
የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ቡድን መሪ አቶ አባድር ፋሪስ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ችግሮቹን ተቋቁሞ ግንባታውን እያካሄደ መሆኑ በመልካምነት የሚነሳ ነው።
መንገዶች ባለስልጣን የካሳ ክፍያ ላይ፣ የምትክ ቦታ በመስጠት በኩል፣ ለ500 ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃና የፋይናስ ችግር ለመፍታት የወሰዳቸው እርምጃዎች በጥንካሬ የሚታዩ ናቸው ብለዋል።
ይሁንና የክፍያ መዘግየት፣ በወቅቱ የመብራት ምሰሶዎችና የውሃ ቱቦ መስመር አለመነሳትና ቅንጅታዊ አሰራሮች ማነስ በክፍተት የሚታዩ ጉዳዮች እንደሆኑም ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት አሁን ባለበት ደረጃ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 70 በመቶ መድረስ ሲገባው አሁን ያለው አፈጻጸም ግን 32 በመቶ መሆኑና ግንባታው መጓተቱን ገልጸዋል።
ስለሆነም ባለስልጣኑ በተቀሩት ጊዜያት የግንባታ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ እንዲያጠናቅቅ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ሙሉጌታ አበበ የፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይም የመብራት ምሰሶና የውሃ መስመር አለመነሳት እንዲሁም ፋይናነስ በወቅቱ አለመለቀቅ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም የመብራት ምሰሶዎችና ከቃሊቲ ከርሰ ምድር መሐል አዲስ አበባ የሚገባውን የ11 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ማንሳት በአፈጣኝ ሊተገበር ይገባዋልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው የመንገዱ ፕሮጀክት ግንባታ ወጪ 50 በመቶ በመንግስት 50 በመቶውን ከቻይና ኤግዚም ባንክ በሚገኝ ብድር ለመገንባት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከገጠማት እዳ የመክፈል ጫና ጋር ተያየዞ መንግስት እንደ አገር በብድር አከፋፈል ላይ እያደረገ ባለው ድርድር አማካኝነት ከባንኩ ማግኘት የነበረበት ገንዘብ ሳይገኝ መቅረቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት 680 ሚሊዮን ብር መድቦ ብድሩ እስኪገኝ ግንባታው እንዳይቋረጥ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የውሃ መስመሩን ለማንሳት ጨረታ ወጥቶ የውል ስምምነት የተደረገ ሲሆን የውሃ መስመሩን የሚያነሳው ተቋራጭ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባም አብራርተዋል።
የወሰን ማስከበርና የመብራት ምሰሶ ማንሳት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የተቀሩትን ቤቶችና የመብራት ምሰሶዎች ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጋር በመሆን የማንሳት ተግባር እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።
የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ታቅዶ ለግንባታውም ሁለት ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል።