ቀጥታ፡

በትንባሆ ላይ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዳማ መጋቢት 23/2011 ትንባሆ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን የጤና ችግር እንዲገታ የቁጥጥር ስራን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና  ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

በትንባሆ  ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር  ማጠናከር  በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት በባለስልጣኑ የትንባሆና  አደገኛ መድኃኒቶች ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ባህሩ ዘውዴ እንዳሉት መንግስት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት አዋጅ  በማውጣት ትንባሆ  በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ዝግጁ ነው፡፡

በአዋጁ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ግልፅ ግንዛቤ አግኝተው ለተግባራዊነቱ  እንዲረባረቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ትንባሆ  ልብ ድካም፣ ካንሰር፣ የሳንባና ሌሎችም የሚያስከትላቸውን መሰል  በሽታዎችን ለመከላከል ከሁለት ዓመት በፊት ብሔራዊ የጸረ ትንባሆ ስትራቴጅክ እቅድ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል፡፡

እቅዱ አሁን ተሻሽሎ ከወጣው ህግ ጋር ቁርኝት እንዲኖረው ግብዓት ለማሰባሰብ ጭምር የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የቀጣዩን አምስት ዓመታት የፀረ ትንባሆ ስትራቴጅክ እቅድ ለመከለስ  እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ቡድን መሪው ይህም  ህዝብ በሚሰበስብበት አካባቢ ትንባሆ እንዳይጨስ ቁጥጥሩን ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ህዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ ትንባሆ እንዳይጨስ ክልከላው 30 በመቶ ላይ የሚገኘውን ሥራ በማስፋፋት 70 በመቶ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።  

እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶችና ሴቶች ትንባሆ እንዳይሸጭ ከመቆጣጠር ሌላ ስለሚያስከትለው ጉዳት በየትምህርት ቤቶች የተማሪ ክበባትን ማደራጀትና በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።

ችግሩን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር  እቅድ በማውጣት ወደ ስራ መገባቱን፣ ህዝብ በሚሰበሰብበትና ሆቴሎች ትንባሆ የሚያጨስ  ማንኛውም አካል በህግ የሚጠየቅበት ዝርዝር መመሪያ መውጣቱም ተመልክቷል።

በዓለም ጤና ድርጅት የትንባሆ ቁጥጥር ተጠሪ ዶክተር ዋሲሁን መላኩ በበኩላቸው በሀገሪቱ በየደረጃው ትንባሆ  የሚያደርሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቀልበስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ  ተናግረዋል፡፡

በትንባሆ ቁጥጥር ሥርዓት  የተሻለ ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ መወስድ እንዲቻልና  የትንባሆ  ንግድ ለማስቀረት ታክስ ከፍ በማድረግ ችግሩን ለማስወገድ  እንደሚያግዙም አብራርተዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ከጤና ፣ ከትምህርት ፣ ከሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች  ሚኒስቴሮችና ከሌሎችም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ተወካዮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ትንባሆ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን የጤና ችግር ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ትርጉም ባለው መልኩ ለውጥ እንዲመጣ  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም