ቀጥታ፡

በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ተካፍሎ በድል ያሸበረቀው የኢትዮጵያ ልኡክ ዛሬ ሌሊት አዲስ አበባ ይገባል

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2011 በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ተካፍሎ በድል የታጀበው የኢትዮጵያ ልኡክ ዛሬ ሌሊት አዲስ አበባ ይገባል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ 5 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 11 ሜዳሊዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አገራት አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሻምፒዮናው 28 አትሌቶችን ጨምሮ በድምሩ 46 የልዑካን ቡድን አባላት ዛሬ እኩለ ሌሊት አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን ነገ ጧት በአራራት ሆቴል እውቅናና ሽልማት ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ውድድሩ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴት 6 ኪሎ ሜትርና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በሁሉም ርቀቶች ላይ ተካፍላለች።

በውድድሩ አምስቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር በአትሌት ሚልኬሳ መንገሻ፣  አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብልና ቀሪዎቹ የወርቅ ሜዳሊያዎች ደግሞ በአዋቂ ሴትና በሁለቱም ጾታ ወጣት ቡድን የተገኙ ናቸው።

ሶስቱ የብር ሜዳሊያዎች በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር በአትሌት ደራ ዲዳ ፣በወጣት ሴቶች በ6 ኪሎሜትር በአትሌት አለሚቱ ታሪኩና በወጣት ወንዶች ደግሞ በአትሌት ታደሰ ወርቁ የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

በአዋቂ ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ በወጣት ሴቶች ፅጌ ገብረሰላማና በአዋቂ ወንዶች የቡድን ውጤት ሶስቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።

በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ67 አገራት የተወጣጡ 582 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር መሳተፍ የጀመረችው ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ጥሩ ውጤትም ከምታስመዘግብባቸው የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል ነው።

ከ1989 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በተካሄዱት የዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ውጤት የሚያሳያው በ1999 ዓ.ም በኬንያ በተደረገ ውድድር ላይ 3ኛ ደረጃን ካጠናቀቅችበት በቀር ባለፉት 18 ውድድሮች ብናይ የአንደኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ነው ያጠናቀቀችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም