የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖን ለመቀነስ የአገራት ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እርምጃ የግድ መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖን ለመቀነስ የአገራት ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እርምጃ የግድ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ መጋቢት 23/2011 የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቀነስ የአገራት ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እርምጃ የግድ መሆኑ ተገለፀ።
ይህ የተገለፀው ለአራት ቀናት የሚቆየውና በማህበረሰብ አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስልት ላይ የሚመክረው ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ ሲጀመር የኢትዮጵያ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ባደረጉት ንግግር ነው።
የበርካታ ታዳጊና የበለፀጉ አገራት ተወካዮች እንደዚሁም ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በተሳተፉበት አውደ ጥናት ላይ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ኢትዮጵያን በመሰሉ ታዳጊ አገራት ላይ እያመጣ ያለው ተፅዕኖ እየበረታ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት በሞዛምቢክ፣ በማላዊና በሌሎች ታዳጊ አገራት እየደረሰ ያለው የጎርፍ አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ታዳጊ አገራት በራሳችን ችግሩን ለመቋቋምና ለመከላከል ቁርጠኝነት ኖሮን ያደጉት አገራት በገንዘብና በቴክኖሎጂ እንዲደግፉን ተፅዕኖ መፍጠር አለብን" ብለዋል።
ታዳጊ አገራት ከተቀረው አለም አቀፉ ማህበረሰበ ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር የአየር ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ለመስራት የሚያስችል ቁጥረኝነት ሊሰንቁ ይገባል ተብሏል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ላለፉት አመታት የተለያዩ የረዥምና የአጭር ጊዜ ፖሊሲዎችን ቀርፃ በመስራትና አለም አቀፍ ተፅህኖ በመፍጠር የሚያበረታታ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይም ድርቅ በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች የእንሰሳት መኖ ባንክ እንዲቋቋም በማድረግ፣ የመኖ ምርትን በመስኖ ለማስፋፋት የተጀመረውን ጥረት አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በተለይ የአርብቶ አደሩን የአደጋ ተጋላጭነት በመቀነስና እሴት የሚፈጠርበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ልምድ ማካፈል የሚችል ተሞክሮ አጎልብታለች ነው ያሉት።
"ይህንን ችግር ለመቋቋም የራሳችንን ቁርጠኝነት በማሳደግ ያደጉ አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጫና ማሳደር የግድ ይለናል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኖርዌይን ጨምሮ የተለያዩ አገራትና ተራድኦ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንና ቃል እየገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በአለም ባንክ የአየር ብክለት መቋቋም ዋና ዳይሬክተር ክርስቲና ጆርጂቪያ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ለማንም የምንተወው ጉዳይ ሳይሆን መላው ዓለምን ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለዚህም ችግሩን ለመቋቋምና ለመከላከል አገራት በራሳቸው የሚያደርጉት ጥረትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የአለም አቀፉም ትብብር ትልቅ ሚና ስላለው ሊጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የአየር ለውጥ የሚያሰከትለውን ተፅእኖ ለመከላከል አገራት እየወሰዷቸው ያለውን መልካም ተመክሮ በማንሳት ልምድ ይለዋወጣሉ፤ እርዳታ ሰጪ አገራት ችግሩን ለመቋቋም መስጠት ባለባቸው ድጋፍ ላይም ይመክራሉ ተብሏል።