ኢሶህዴፓ ለውጡን የሚያስቀጥሉ አመራሮችን ወደፊት ሊያመጣ ይገባል.... የፓርቲው ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
ኢሶህዴፓ ለውጡን የሚያስቀጥሉ አመራሮችን ወደፊት ሊያመጣ ይገባል.... የፓርቲው ሊቀመንበር
ጂግጅጋ መጋቢት 23/2011 የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ሀገራዊና ክልላዊ ለውጡን በተፈለገው መልኩ ማስቀጠል የሚችሉ አመራሮችን ወደፊት ሊያመጣ እንደሚገባ የፓርቲው ሊቀመንበር ተናገሩ።
የፓርቲው አስረኛ ድርጅታዊ ጉባዔ " ሁለንተናዊ ለውጥ ለክልሉ ልማት፣ ፍትህና አንድነት" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ካሊ አዳራሽ ተጀምሯል።
ፓርቲው በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ያጋጠመውን አደጋ ለመወጣት መዋቅራዊና የውስጥ ማሻሻያ ሪፎርም መጀመሩ ተመልክቷል።
በጅግጅጋ ከተማ ካሊ አዳራሽ በተጀመረው ጉባኤ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት ፓርቲው የክልሉን አርብቶ አደር ህዝብ በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
በእዚህም ውጤት ቢመዘገብም ባለፈው ሐምሌ ወር በፓርቲው መሪዎች የተፈፀመው ስህተት በህዝቡ ላይ ቅሬታና መጠራጠር መፍጠሩን ተናግረዋል።
በእዚህም በርካታ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጭምር ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።
በአስረኛው ድርጅታዊ ጉባኤም በእነዚህ የፓርቲ አመራሮች የሚተኩ አመራሮች እንደሚመረጡ ገልጸው የጉባኤው አባላት ሀገራዊና ክልላዊ ለውጡን በተገቢውና በተፈለገው መልኩ ማስቀጠል የሚችሉ አመራር አካላትን ወደ አመራርነት ሊያመጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ለፓርቲያቸውና ለህዝቡ ጠንካራ አመለካከት ያላቸውን በመምረጥ ድርጅቱ ክልሉን የመምራት ኃላፊቱን በተሻለ ሁኔታ እንዲወጣ ማገዝ ይኖርባቸዋል" ሲሉም ገልጸዋል።
ለፓርቲው ውስጥ ደንብ ተገዢ የሆኑና የፖለቲካ መርሀ ግብሩን ለማስፈጸም ቁርጠኛ የሆኑ አካላት እንዲመርጡ የጉባኤው አባላት የጋራ ግንዛቤ ወሳኝ መሆኑንም አቶ አህመድ ጠቁመዋል።
ዛሬ በተጀመረው ጉባኤ ላይ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 700 ተሳታፊዎች በድምጽ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በታዛቢነት የተሳተፉ ናቸው ተብሏል።
በጉባኤው በርካታ አዳዲስ ወጣት ምሁራን በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትና በሥራ አስፈጻሚ አመራርነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በድርጅቱ ጉባኤ ላይ ኢህአዴግን በመወካል የአጋርነት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው ፓርቲው ካጋጠመው ችግር ወጥቶ ራሱን ለማረም የለወጥ ሀይሎችን ማሳተፉ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ኢህአዴግ ኢሶህዴፓን ጨምሮ አምስቱን አጋር ድርጅቶች አካቶ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ጥናት እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግን (ሐብሊ) እና ሌሎች ፓርቲዎች ተወካዮች ለኢሶህዴፓ ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።