በስምንት ወራት 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ አገሮች የገንዘብ ኖት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተይዟል - ኢዜአ አማርኛ
በስምንት ወራት 100 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ አገሮች የገንዘብ ኖት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተይዟል
አዲስ አበባ መጋቢት 23/2011 ባለፉት ስምንት ወራት የ100 ሚሊዮን ብር የምንዛሬ መጠን ያለው የተለያዩ የውጭ አገሮች የገንዘብ ኖት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቦሌ ጉምሩክ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለፉት ስምንት ወራት ያከናወነውን ተግባር በተመለከ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሪፖርቱን አቅርቧል።
የጉምሩክ ቅርጫፉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን 625 ሺህ በላይ የብር የምንዛሬ መጠን ያለው የተለያዩ አገሮች ገንዘብ ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተመሳሳይም ወደ አገር ሊገቡ የነበሩ ከ115 ሚሊዮን 170 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት 8 ወራት ውስጥ 48 ነጥብ 40 ኪሎ ግራም ኮኬይን አደንዛዥ ዕጽ ከተለያዩ አገሮች ተነስቶ በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ሶስተኛ አገር ሊተላለፍ ሲል ከነአዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
ያለመፈተሽ መብት ባላቸው በአፍሪካ ህብረት፣ በሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን ኢምባሲና ዲፕሎማቶች ስም የገቡ በአጠቃላይ 61 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ህገወጥ ዕቃ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በዚሁ ጊዜ ውስጥ ቀሪ ዕዳ ያለባቸውና በቦንድ ዋስትና አስገብቶ ግዴታቸውን ካልተወጡ ድርጅቶች ከ46 ሚሊዮን 115 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዚሁ ወቅት 23 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ ከሽያጭ የተገኘ ሲሆን 27 ነጥብ 75 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ጊዜ ያለፈባቸው ዕቃዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲወድም መደረጉን ገልጸዋል።
ከተለያዩ ተሽከርካሪዎች ቀረጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ 919 ሚሊዮን 267 ሺ ብር በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
የኤክስ ሬይ ማሽን ብዛት ስሌላቸውና ያሉትንም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአግባቡ ያለመጠቀም፣ ያለመፈተሽ መብት ያላቸው ዲፕሎማቶች በኮንትሮባንድ መሳተፍ፣ የኢትዮጵየ አየር መንገድ ዕቃዎችን ቶሎ ለይቶ ያለማስረከብና ሌሎች ችግሮች በዕቅድ መሰረት ለመስራት እንዳላስቻሉ አቶ ተገኔ ገልጸዋል።
በተለይ ያለመፈተሽ መብት ያላቸው ዲፕሎማቶች ጉዳይን በሚመለከት ምክር ቤቱ እንዲያግዛቸው አቶ ተገኔ ጥሪ አቅርበዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም ግብረ መልሱን ሌሎች ጉብኝቶችን ካደረገ በኋላ ከነገ በስቲያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።