በኢትዮጵያ ፖለቲካና በአገር ዕድገትና ልማት ላይ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ታይተዋል-የፖለቲካ ፓርቲ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፖለቲካና በአገር ዕድገትና ልማት ላይ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ታይተዋል-የፖለቲካ ፓርቲ አባላት
አዲስ አበባ መጋቢት 23/2011 ባለፈው አንድ ዓመት በፖለቲካ ፣ በዲፕሎማሲ ፣ በአገር ዕድገትና ልማት ላይ ተስፋ ሰጪ ተግባራት መታየታቸውን በውጭ አገሮች ሲንቀሳቀሱ ቆይተው ወደአገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተናገሩ።
በሌላ በኩል ዘረኝነትና ብሄርተኝነት የተስፋፋበት፣ የዜጎች መፈናቀልና የህግ ጥሰት በስፋት የተስተዋለበት ዓመት መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ኢዜአ የፓርቲዎች አባላትን አነጋግሯል።
የሲዳማ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ካሳ አየለ እንዳሉት መንግስት ባለፈው አንድ ዓመት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ከሌሎች አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያከናወነው ተግባር ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዚያት ለአገሪቷ አንድነትና ዕድገት የሚጥሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች ከአገር እንዲሰደዱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁና ለእስርና እንግልት መዳረጋቸውን አስታውሰዋል።
ከአገር የተሰደዱ የፓርቲ አባላት ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ፣ ከእስር እንዲፈቱና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ መንግስት ሰፊ ተግባር ማከናወኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና ፓርቲዎቹ በቅርበት በመወያየት የተሻለ አገር ለመፍጠር በመንግስት በኩል የተደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን በአዲስ መልክ በማዋቀር ፓርቲዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የተሰራው ስራ ለፓርቲዎች ጥያቄ መልስ የሰጠ እንደሆነ አመልክተዋል።
ፓርቲዎቹ የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚችሉትና የህዝብን ድምጽ ሊወክሉ የሚችሉት ተዋህደው ሲሰሩ መሆኑን በማመን መንግስት የተበታተኑትን ፓርቲዎች ለማሰባሰብ የጀመረው ጥረት መጠናከር እንደሚኖርበት አቶ ካሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረ ህዝብ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ አስካለ ሃይሌ በበኩላቸው መንግስት የዲፕሎማሲ ጥረቱን በማጠናከር ከጎረቤትና ከሌሎች አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ሰፊ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
የአገሪን ኢኮኖሚ ለመታደግ ከተለያዩ አገሮች ጋር የተደረገው ስምምነት አገርን ከመበታተንና የህዝቦች የኑሮ ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይወርድ መደረጉን ገልጸዋል።
ነገር ግን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በወሰደው የተለሳለሰ አካሄድ ዘረኝነትና ብሄርተኝነት እንዲስፋፋና የዜጎች መፈናቀልና እንግልት እንዲስፋፋ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለዜጎች ህይወት መጥፋት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መንግስት መስራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
አገሪቷን ከረዥም ጊዜ ችግሮች ለመላቀቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እገዛና ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የተናገሩት ወይዘሮ አስካለ ፓርቲያቸው የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።