የኢትዮጵያ የስነ አካባቢ ጥበቃ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በትግራይ ክልል ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የስነ አካባቢ ጥበቃ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በትግራይ ክልል ይከበራል
መቀሌ ግንቦት 24/2010 የኢትዮጵያ የስነ አካባቢ ጥበቃ ቀን " የፕላስቲክ ብክለትን እንከላከል" በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ በትግራይ ክልል እንደሚከበር ተጠቆመ። በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ በርሄ ፍስሃ እንዳሉት ኤጀንሲው ከአካባቢ ደን ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትርና ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የስነ አካባቢ ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል። የቀኑ መከበር የአየርና ውሃ ብክለትን በመከላከልና አካባቢን በማይጎዳ መልኩ በመጠቀም ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ አንደሚቻል ሕብረተሰቡን የማነሳሳት ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል። ከእዚህ በተጨማሪ ስነ አካባቢን የቀጣዩ ትውልድ ፍላጎትና ጥቅምን በሚያስጠብቅ መልኩ በመጠቀም አካባቢን ከውድመት የመከላከልና የመሬት መሸርሸርን የመከላከል አላማ ይዞ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት። ቀኑ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ሕብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ በስነ አካባቢ ጥበቃ ስርዓት ላይ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡና በእዚህም አካባቢውን በመንከባከብ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል። የቀኑ መከበር በየአካባቢው የሚገኝ ማህበረሰብ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ፣ በችግኝ ተከላ፣ በደን ጥበቃ፣ ህገወጥ ግጦሽ በመከላከል በስፋት ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። "በዓሉ ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በአካባቢ ጥበቃ ተገቢውን ግንዛቤ አግኝተው የድርሻቸውን እንዲወጡ አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተሞክሮና ልምድ የሚቀሰምበት ይሆናል" ብለዋል። በበዓሉ ላይ ከፌደራል መንግስት፣ ከክልሎችና ከዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በዓሉም በፓናል ውይይትና በትግራይ ክልል የአረንጓዴ ልማትን በማቀጣጠል ዓለም አቀፍ የወርቅ ሽልማት ባገኘችው የአብርሃ ወ-አጽብሃ ገጠር ቀበሌ የመስክ ጉብኝት በማድረግ እንደሚከበር ታውቋል። በመጪው ግንቦት 27 እና 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሚከበረው በዚህ በዓል ላይ ከ400 በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።