ህብረተሰቡ መረጃና እውቀት ለማግኘት የንባብ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበት ተመለከተ

92

ጅማ መጋቢት 22/2011 ህብረተሰቡ መረጃ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን እውቀት ለመቅሰም  የንባብ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበት ተመለከተ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽህፍት ኤጀንሲ ከጅማ ዩኒቨርስቲና ከጅማ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባባር "ማንበብ ሙሉ ሰው ያደረጋል " በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት  ተጀምሯል፡፡

የንባብ ሳምንቱን ትናንት መርቀው ያስጀመሩት የኤጀንሲው  ዋና ዳይሬክተር አቶ ይክኑአምላክ መዝገቡ " ንባብ በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ታላቅ ሚና አለው" ብለዋል፡፡

ያዘጋጁት የንባብ ሳምንት ዓላማም የህዝቡን የንባብ ባህል ማሳደግ፣ ህብረተሰቡ ለመረጃ ሀብት ያለውን ግንዛቤ ማስፋት ፣ የጽሁፍ ሀብትና ቅርስን ጠብቆ ለማቆየት መነሳሳትን ለመፍጠር ነው፡፡

እንዲሁም ለህትመት ኢንዱስትሪው ፣ ለደራሲያንና በዘርፉ ለሚገኙ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሆነም ተገልጿል፡፡

" በአሁኑ ወቅት   ሰዎች እንደ ፌስቡክ ከመሰሉ መረጃዎችን ለማግኘት ምርጫቸው ሲያደረጉ በስፋት ይታያሉ" ያሉት ዳይሬክተሩ ሆኖም  እነዚህ የመረጃ ምንጮች በአብዛኛው  ዕውቀት የሚገኝባቸው እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ መረጃ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን እውቀት ለመቅሰም  የንባብ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

መስሪያ ቤታቸው የህብረተሰቡ የንባብ ባህል ለማሳደግ   ከተለያዩ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን  ጠቅሰዋል፡፡

ከጥረታቸውም ውስጥ ከጅማ ዩኒቨርስቲና ጅማ ከተማ አስተዳደር  ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር እስከ 25/2011 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ የንባብ ሳምንት ማዘጋጀታቸው መሆኑን  አቶ ይክኑአምላክ አስረድተዋል፡፡

በተጓዳኝም  የስነጹሁፍ አውደርዕይ፣የመጸሐፍት  ሽያጭና የፓናል ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

በጅማ ከተማ በተዘጋጀው የንባቡ ሳምንት የመክፈቻው ስነስርዓት የአካባቢው አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ ደራሲያንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም