ቀጥታ፡

'ከመጋቢት እስከ መጋቢት' የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት በፎቶግራፍ ተሰነደ

አዲስ አበባ  መጋቢት22/2011 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት በፎቶግራፍ በመሰነድ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

'ከመጋቢት እስከ መጋቢት' የተባለ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ዛሬ ጠዋት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።

የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለ ሲመት ካደረጉበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ድረስ በአገር ውስጥ፣ በምስራቅ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮጳ አገሮች ያከናወኗቸውን ተግባራት የሚያሳይ ነው።   

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ የለውጡን አንደኛ ዓመት ከማክበር ባሻገር የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ የአገሪቷን ታሪክ ከስር ከስሩ እየሰነዱ ለትውልድ ማስቀመጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው።

''ለምን አይናገር ይናገራል ፎቶ ትዝታን አስታውሶ ትዝታን ጎትቶ'' የሚለውን አገራዊ ብሂል የተጠቀሙት ዶክተር ሂሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት በተገኘው ለውጥ ምን ሰራን? የት ነበርን? ምን አደረግን? ለሚለው ከንግግር በላይ ፎቶግራፍ ገላጭ መሆኑን አብራርተዋል።

በፎቶግራፍ ጥበብ የአገሪቷን ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሲሆን በወቅቱ ያልተሰነደን ታሪክ ከሃምሳና ከመቶ ዓመት በኋላ ለመፈለግ አስቸጋሪ እንደሆነም ገልጸዋል።

የፎቶግራፍ ጥበብን በመጠቀም በአገሪቷ ያለው ታሪክ ለትውልድ በሚተላለፍበት ወቅት በወቅቱ ስንጠቀም የነበረውን ቴክኖሎጂ፣ የባለሙያዎችን የእውቀትና የክህሎት ደረጃ ለማሳየት የሚረዳ እንደሆነም ገልጸዋል።

በአውደ ርዕዩ 'የፎቶ ዘገባ ታሪካዊ ፋይዳ ካለፉት የለውጥ ሂደቶች አንጻር ምን ይመስላል?' በሚል ርዕስ ላይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የስነ-ጥበባት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የስነ-ጥበባት ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እና የፎቶግራፍ ባለሙያ አይዳ ሙሉነህ የውይይት ሀሳብ አቅርበዋል።   

በኢትዮጵያ ከተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጠንካራ ጎን ለመማርና ድክመቶችን ለማረም እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦችን ለመጨመር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውም ተገልጿል።

መጋቢት 13 እና 14 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት 'አዲስ ወግ' በሚል ርዕስ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደትን የሚገመግም የውይይት መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ 'የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ፣ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮቶች'፣ 'የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ'፣ 'የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሥራ ፈጠራና ማህበራዊ አካታችነት' እንዲሁም 'የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ማጽናት በኢትዮጵያ፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አካሄዶች' በሚል ሐሳብ ላይ ውይይት ተካሂዷል።  

በተመሳሳይ መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም መንግስት በአምስት ዘርፎች ላይ ባከናወናቸው ተግባራት ላይ የባለሙያዎች ውይይት ተደርጓል።

ከነገ መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፍ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለ ሲመት ያደረጉበትን ቀን ለማሰብ ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ህዝባዊ ውይይት ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።

ባለፈው አንድ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጓቸውን ንግግሮች በማሰባሰብ አንድ መድብል ተዘጋጅቶ ለታሪክ በኢትዮጵያ ባሉ ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በአብያተ መጻሕፍት እና ከዚህ ጋር ተያያዥ ሙያ ላላቸው ተቋማት ለታሪክ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

ለውጡን በተመለከተ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ምሁራን ያደረጓቸው ጥናቶች በጆርናል እንዲታተም በማድረግም ከመጋቢት እስከ መጋቢት ያለው የለውጥ ሂደት መርሐ ግብር ማጠናቀቂያ እንደሚሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም