በአገር አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ኋይለማሪያም ኪሮስና አትሌት ስንቄ ደሴ አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በአገር አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ኋይለማሪያም ኪሮስና አትሌት ስንቄ ደሴ አሸነፉ
አዲስ አበባ መጋቢት 22/2011 በቢሾፍቱ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች አትሌት ኋይለማሪያም ኪሮስ፤ በሴቶች ደግሞ አትሌት ስንቄ ደሴ አሸነፉ።
ዛሬ በተካሄደው ውድድር ከ20 በላይ ተለያዩ ክለቦችና ክልሎች የተውጣጡ 279 ወንዶችና 109 ሴቶች በድምሩ 388 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በወንዶች የተደረገውን ውድድር አትሌት ኋይለማሪየም ኪሮስ ከኦሮሚያ ፖሊስ 1 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ3 ሴኮንድ በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ክለብ አትሌት የሆነው ለሚ ዱሜቻ ደግሞ በ1 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ደግሞ በግል የተወደዳረው አትሌት ገብሬ ሮባ ሲሆን ርቀቱን ለመጨረስም 1 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ13 ሴኮንድ ወስዶበታል።
በሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ የፌዴራል ማረሚያ ቤት አትሌቷ ስንቄ ደሴ በ1 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ አንደኛ መሆን ችላለች።
አትሌት ፀሃይ ደሳለኝ 1 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ8 ሴኮንድና አትሌት ውባለም ባሳዝነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ሰዓት ከ 15 ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በዚህ ውድድር በቡድን ውጤት በወንዶች ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንደኝነት ማጠናቀቅ ችለዋል።
በውድድሩ በሁሉም ጾታ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ የወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው ከ20 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ከታዋቂ አትሌቶች መካከል አትሌት የማነ ፀጋዬ በውድድሩ ላይ ተሳትፎ 33ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ከውድድሩ በኋላ አትሌት የማነ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበረው ቆይታ ውድድሩ ብዙ ወጣት አትሌቶች እየመጡ መሆኑን የሚያሳይ ፉክክር ነበር ብሏል።
በውድድሩ ላይ አየሩ ሞቃታማ በመሆኑና የጉንፋን ህመም ተጨምሮበት ጥሩ ውጤት እንዳያመጣ ምክንያት እንደሆነበትም ነግሮናል።
በውድድሩ አዝናኝ የነበረው በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር አንደኛ ሆኖ የሚገባው አትሌት አጨራረስ ላይ በሁለት ስዎች የሚያዘውን ሪባን አትሌቱ ይዞት መግባት ሲገባው ከፊት ሆኖ አትሌቶችን ይመራ የነበረው ሞተረኛ ሪባኑን ይዞ መግባቱ በብዙዎቹ ተመልካቾች ዘንድ ፈገግ ያሰኘ ክስትተ ነበር።