የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ

167
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 በመላው አገሪቱ ሲሰጥ የነበረው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ገለፀ። ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ 1ሚሊዮን 222 ሺህ 757 የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች ለሶስት ቀናት በመላ አገሪቱ በሚገኙ 2 ሺህ 709 ፈተና ጣቢያዎች ተፈትነዋል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፤ ለ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና ሞባይል ይዞ ወደ ፈተና ጣቢያ ለመግባት መሞከር፣ ለሌላ ሰው ለመፈተን መሞከር ከመሳሰሉ ጥቃቅን ተግዳሮቶች በስተቀር ችግር አላጋጠመም። በአገሪቱ የተፈጠረው የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል። ተማሪዎች፣ ወላጆች፣መምህራን፣ በየደረጃው ያሉት የትምህርት ማህበረሰቦችና የፀጥታ ሀይሎች ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ኤጀንሲው ምስጋና አቅርቧል። መምህራን ከማስተማር በተጨማሪ ስለፈተና ዲሲፕሊን ሲያስተምሩ በመቆየታቸውም ተማሪዎች በራስ መተማመን እንዲፈተኑ ያገዛቸው መሆኑን ዶክተር ዘሪሁን ተናግረዋል። የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሰኞ ጀምሮ ለአራት ቀናት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፈተናው በሚፈለገው መልኩ እንዲካሔድም ተመሳሳይ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ፈተናው እስኪጠናቀቅ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራንና ሁሉም ማህበረሰብ የተለመደ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ዘንድሮ 284 ሺህ ተማሪዎች ከመሰናዶ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ይወስዳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም