ቀጥታ፡

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በደረሰ ቃጠሎ 311 ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ወደመ

ጎንደር መጋቢት 22/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በደረሰ የእሰሳት ቃጠሎ 311 ሄክታር የሚሸፍን የተፈጥሮ ሀብት መውደሙን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ላለፉት ሶስት ቀናት የቆየው የእሳት ቃጠሎ በህዝብ ተሳትፎ ትላንት ምሽት  በቁጥጥር ስር መዋሉም ተመልክቷል።

የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደገለፁት በቃጠሎው በፓርኩ እሜት ጎጎ በተባለ ቦታ 311 ሄክታር የተፈጥሮ ደን ሙሉ ለሙሉ  ሲወድም ሳንቃ በር በተባለ ቦታ ደግሞ 31 ሄክታሩ በከፊል ጉዳት ደርሶበታል።

በአካባቢው መጣል የጀመረው ዝናብ የተፈጠረው ቅዝቃዜ ቃጠሎውን በመቆጣጠር ሂደት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ።

"ቃጠሎው ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይሰፋፋ የደባርቅ፣ የዳባት፣ የጃናሞራና የጎንደር ከተማ ወጣቶችና ነዋሪዎች እንዲሁም የጎንደርና የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረጉት የመከላከል  ስራ ከፍተኛ ግምት  ተሰጥቶታል" ብለዋል ።

"የደባርቅ የቱሪስት አስጎብኚ ማህበራት አባላትና የጸጥታ ኃይሉም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር" ያሉት ኃላፊው ሆቴሎችና ምግብ ቤቶችም ቃጠሎውን ለማጥፋት ለተሰማራው ህብረተሰብ ምግብና ውሃ በማቅረብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ2ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት ተሳትፎ ቃጠሎውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ የቃጠሎውን መንስኤ የሚያጠና ግብር ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም