ቀጥታ፡

ግን ለምን?

አዲስ አበባ  መጋቢት 21/2011 ''ተጎጂ እኛ፣ ጉዳት አድራሽ እኛ፣ ተከላካይ እኛ፣ ተመልካች እኛ ግን ለምን?''

ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም መምህር የሆኑት ዶክተር ዳንኤል ገብረእግዚሃብሄር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ የመነሻ ጽሁፋቸውን ባቀረቡበት ወቅት ነው።

የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የከተማዋ የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተገኙበትና በአገሪቱ የሚታየውን የሰላም እጦት መንስኤ በመለየት መፍትሄ ለማፈላለግ የሚረዳ ውይይት ዛሬ ተደርጓል።  

ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ መሆኑን ያወሱት ዶክተር ዳንኤል ፖለቲከኞች ተማሪዎችን እንደ ዋንኛ መሳሪያቸው የሚጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች 28 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች እንደሆኑና በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ናቸው።

ቴክኖሎጂውን ለመልካም ተግባራት የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ፣ በማህበራዊ  ሚዲያ ያልተፈለጉ መልዕክቶችን፣ የሃሰት መረጃዎችንና ሰላምን የሚሸረሽሩ ሃሳቦችን በማሰራጨት ግጭት የሚቀሰቅሱ መኖራቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የግጭት መንስኤ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር መሆኑንም ገልጸዋል።

ግለሰቦችና ቡድኖች ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ ሲገባቸው የግል ጥቅማቸውን ለማራመድ በተማሪዎች እንደሚጠቀሙ ተቀምጧል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዜጎቿ እያጣች ያለውን ሰላም ለመመለስ የመምህራን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ''ኢትዮጵያ ውስጥ መጥፎም ጥሩም እሴቶች አሉን ጥሩውን እንዴት አጎልብተን መጠቀም እንዳለብን ግን ገና አልደረስንበትም'' ብለዋል።

መልካም የሆኑት የመረዳዳት፣ አገር መውደድ ፣ ጀግንነትና ትህትና፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ቤተሰባዊነት እንዲሁም የሰው አክባሪነት እሴቶቻችን በመሸርሸራቸው ለአገሪቱ የሰላም መጥፋት ሰላም አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ አንስተዋል። 

በርካታ ተሳታፊዎች የቀረበውን ሃሳብ በመንተራስ ሰላምን በማህበራዊ እሴቶች በመታገዝ ለመመለስ በተለይም በመምህራን በኩል በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ሊሰራበት የሚገባ እንደሆነ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የጉለሌ መምህራን ማህበር አባል የሆኑት መምህር ታደሰ ስዩም፤ ''ቀደምት አባቶች በሰላምና በአንድነት ጠብቀው ያቆይዋት አገር ዛሬም በዜጎቿ መጠበቅ አለባት፣ በተለይም መምህራን አገር ተረካቢዎችን እንደማፍራታችን ከፍተኛ ሃላፊነት አለብን'' ብለዋል።

መምህር ሙሉዓለም ኃይሌ ከየካ መምህራን ማህበር ባነሱት ሃሳብ ደግሞ፣ ''ማንኛውም ሰው ያለ ሰላም መኖር እንደማይችል ስለሚታወቅ የሚጠበቅብንን ማድረግ ይገባናል፣ በተለይ መምህራን ተማሪዎቻችንን በመልካም ስነ ምግባር በማነጽ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን'' ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የመጡ ተማሪዎች በበኩላቸው እንዲህ ባለው መድረክ መሳተፋቸው አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዱ እንዳደረጋቸው ገልጸው፣ በእነሱ በኩልም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል።

ጥሩ የሚባሉትን አገራዊ እሴቶችን በማጎልበት፣ የአገሪቷን ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት ለማስፈንም የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉ በውይይቱ የታደሙ ባለድርሻ አካላት ተናግረዋል።

በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሰላምን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ቀጣይነት እንዲኖረው ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም