ቀጥታ፡

አዲስ የጦር መሳሪያ አያያዝ ህግ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 አዲስ የጦር መሳሪያ አያያዝ ህግ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የጸረ-ጥላቻ ንግግር አዋጅ እንደተዘጋጀና በጥቂት ጊዜያት ለህዝብ ውይይት እንደሚቀርብ ተቋሙ አስታውቋል።

ይህ የተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያዘጋጀውና ከመጋቢት 2010 ዓም እስከ አሁን የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ለውጦች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት ነው።

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ አያያዝ የሚመራበት ግልጽ ህግ የላትም።

ይህ ክፍተት በዜጎች ወጥቶ መግባት ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረ መንግስት መረዳቱን ጠቁመው፤ ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል አዲስ የጦር መሳሪያ አያያዝ ህግ በቅርቡ ይተገበራል ነው ያሉት።

በአገሪቱ ከሚታየው ልቅ የጦር መሳሪያ አያያዝ በተጨማሪ በተለያዩ ዘዴዎች እየተሰራጨ ያለው የጥላቻ ንግግር ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል ነው ያሉት።

መንግስት ከተለያዩ አገሮች ልምድን ቀምሮ የጥላቻ ንግግርን መግራት የሚያስችል አዋጅ ማዘጋጀቱን የጠቆሙት ምክትል አቃቤ ህጉ፤ አዋጁ ህዝብ እንዲወያይበት ተደርጎ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዲስ ከሚያወጣቸው አዋጆች በተጨማሪ የጸረ-ሽብርን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም