"ለውጡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከውድቀት ታድጓል" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ  መጋቢት 21/2011 አገራዊ ለውጡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከውድቀት የታደገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የግድቡ ግንባታ የሚገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ አቋም ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሪፖርት በግድቡ ዙሪያ ከሚሰሩ ኮሚቴዎች ቀርቦ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየትና መመሪያ ተሰጥቶበታል።

የግድቡን ወቅታዊ አቋም በሚቃኘው ግምገማ፤ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ፤ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ድርድር፤ የአባይ ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ እና የግድቡ ሙሌት ደረጃ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት በአሁኑ ወቅት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ እየሰራ ነው ብለዋል።

ማኔጅመንቱ ጠንካራ ውሳኔ በማሳለፍ ግድቡን ከውድቀት መታደጉን ገልፀው በተቀመጠለት ጊዜና በጥራት እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከውይይቱ በኋላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የነበሩ ችግሮች ተፈትተው ወደ ተግባር ተገብቷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ በመንግስት በኩል በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ምክንያት የነበሩ ችግሮች ተፈተው ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ የሲቪል ሥራዎች አፈፃፀም 83 በመቶ፤ የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራዎች 25 በመቶ፤ ሀይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር 13 በመቶ ሲሆን አጠቃላይ አማካይ አፈፃፀሙ 66 በመቶ ነው።

የግድቡ ግንባታ ሲጀመር 80 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተያዘ ቢሆንም አሁን 98 ነጥብ 7 የገንዘብ ክፍያ አፈፃፀም አለው፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ 150 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገልጿል።

አሁን በተደረገው የለውጥ እርምጃ ግድቡ ግንባታው ሳይጠናቀቅ በታህሳስ ወር 2013 ዓም ሁለት ተርባይኖችን በመጠቀም ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም