ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ - ኢዜአ አማርኛ
ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
ባህር ዳር መጋቢት 21/2011 በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ከ18 ዓመት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግል የነበረው ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
የጋዜጠኛ መዝሙር የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ ከቀኑ 5፡00 በባህር ዳር ደብረ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን የሥራ ባልደረቦቹ፣ አድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት ተፈጽሟል።
ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ከአባቱ ከአቶ ሐዋዝ ከበደ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ካሳየ ማዘንጊያ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ ሞጣ ከተማ የተወለደው በ1962 ዓ.ም ነው ።
ዕድሜው ለትህምርት ሲደርስ በሞጣ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ከጎንደር መምህራን ኮሌጅ ማሰልጠኛም በ1982 ዓ.ም በመምህርነት ሙያ ተመርቋል።
ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በመምህርነት ሙያ ህዝቡን ካገለገለ በኋላ ከ1989 እስከ 1992 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ትምህርት መገናኛ ዘዴዎች የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ መስራቱን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።
ከእዚህ በተጨማሪ በምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በዜና ሪፖርተርነት ለአንድ ዓመት ሰርቷል።
ጋዜጠኛ መዝሙር ሃዋዝ ከ1993 እስከ 2003 ዓ.ም በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ባሉ የሥራ መደቦች አገልግሏል።
ከ2003 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮም የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሕይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ለድርጅቱ መለወጥና ማደግ በቅንነትና በታታሪነት ሲያገለግል መቆየቱ በሕይወት ታሪኩ ላይ ተገልጿል።
በቆይታውም ድርጅቱ የሚመራበትን ኤዲቶሪያል ፖሊሲን ጨምሮ የተለያዩ መመሪያዎችና አሰራሮችን በመቅረፅና በማዘጋጀት ተቋሙን በተሻለ ኃላፊነት አገልግሏል።
የድርጅቱ መመሪያዎች ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲሄዱ ለማድረግ ዳግም የማሻሻልና ተጨማሪ አዳዲስ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ እንደነበርም የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።
"የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ እድገት የምዕተ ዓመት ቅኝትና የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ" በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍም ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በጋዜጠኝነት ሙያ በዲፕሎማ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት የመጀመሪያና 2ኛ ዲግሪውን ተከታትሎ አጠናቋል።
ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ በአጋጠመው የጤና ዕክል በተለያየ ጊዜ ሕክምና ሲደረግለት ቢቆይም ጤናው እየተሻሻለ ባለመምጣቱ በተወለደ በ49 ዓመቱ መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር።