የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአገሪቱን ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በኃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአገሪቱን ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በኃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ
አዳማ መጋቢት 21/2011የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የአገሪቱን ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በኃላፊነት እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አሳሰበ።
ባለሥልጣኑ በሰላም ጋዜጠኝነትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ለሴት የሚዲያ ባለሙያዎች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የሚዲያ ልማትና ብዝኃነት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ በዚሁ ወቅት እንዳስታወቁት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ ባለሙያዎቹ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል።
ባለሙያዎቹ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ከመዘገብ ባለፈ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያላቸውን የልማት፣የሰላምና በዜጎች መካከል መቀራረብና አንድነት እንዲጠናከር ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ መረጃ ለኅብረተሰቡ እንዲያደርሱም አሳስበዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶች ተባብሰው እንዲቀጥሉ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ከመስራት በመቆጠብ አንድነትንና የጋራ አስተሳሰብ በሚፈጥሩ ዘገባዎች ላይ እንዲያተኩሩ ጠቁመዋል።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ቋማትና ባለሙያዎች በተሳሳተ መረጃ ኅብረተሰቡን እያደናገሩ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ከተሳሳተ ድርጊታቸው ተቆጥበው በብሮድካስትና በፕሬስ ሕጉ በተቀመጠው ሥነ ምግባር መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ከሥነ ምግባር ውጭ በሚንቀሳቀሱት አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኤፍ ኤም 100ነጥብ5 ጋዜጠኛ እሰይ ብርሃኑ በማህበራዊ ድረ ገጽና በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከሚተላለፉ ዘገባዎች ሕዝቡ ማግኘት የሚገባውን ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ እንደማያገኝ ተናግራለች።
ችግሩን ለመፍታት ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች እንደሚጠበቅ አመልክታለች።
የሪፓርተር ጋዜጣን በመወከል በውይይቱ እየተሳተፈች የምትገኘው ሻሂዳ ሁሴን በበኩሏ መገናኛ ብዙኃን ለሕዝቡ ወቅታዊና ጠቃሚ መረጃ ከማድረስ አንጻር ውስንነቶች አሉባቸው ገልጻለች።
በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚለቀቁ የሕዝቡን የተረጋጋ ኑሮ የሚያደፈርሱ፣በህዝቦች መካከል ዘላቂና የማይሻር ቁርሾ እንዲፈጠር የሚተጉ አካላትን በመተቸት ለአገር የሚበጀውን አቅጣጫ መጠቆም ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች እንደሚጠበቅ አመልክታለች።
ዛሬ በሚጠናቀቀው በዚሁ የውይይት መድረክ ከአዲስ አበባና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ሴት ጋዜጠኞች እየተሳተፉ ነው።