የስኳር ህመም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወታችን ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል-- ህሙማን - ኢዜአ አማርኛ
የስኳር ህመም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወታችን ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል-- ህሙማን
አዲስ አበባ መጋቢት 21/2010 የስኳር ህመም በጤናቸው ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ነው አስተያየታቸውን የሰጡ ታማሚዎች የገለፁት።
የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ካሳሁን አበበ የስኳር ህመምተኛ ከሆኑ ላለፉት አምስት ዓመታት ኢንሱሊን እየገዙ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ ፡፡
የኢንሱሊን መርፌን ከሁለት መቶ ብር በላይ እየገዙ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት አቶ ካሳሁን ወጪው በኑሯአቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው ነው የሚጠቅሱት።
የደሞዝ ተከፋይ በመሆናቸው እየተቸገሩም ቢሆን ኢንሱሊን እየገዙ እየተጠቀሙ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ካሳሁን በርካታ የመግዛት አቅምየሌላቸው የስኳር ህመምተኞች እንዳሉ መታዘባቸውን ይናገራሉ።
“ኢንሱሊንን ሆነ ሌሎች የህመሙ መድሀኒቶችን በነጻ ለማግኘት የሐኪም ማረጋገጫ፤ ከቀበሌ ድጋፍ ያስፈልጋል፤ ይህ አግባብ አይደለም” ሲሉየተናገሩት አቶ ካሳሁን ታካሚዎቹ ክትትል በሚያደርጉበት ሆስፒታል መድሃኒቱን በነጻ ለመውሰድ ሲመጡም በአግባቡ እንደማይስተናገዱ ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳም የስኳር ህመምተኞቹ መድሀኒቱ ያልቅብናል በሚል ስጋት በታዘዘላቸው መሰረት ሳይሆን መድሀኒቱን ቆጥበው እንደሚወጉ ከታማሚዎቹ መስማታቸውን ያስረዳሉ።
ህመሙ ከጤና በተጨማሪ በማህበራዊ ህይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ የሚናገሩት ሌላው የስኳር ታማሚ አቶ ዳዊት ግርማ፤ህመሙየሚያነጫንጭ ከመሆኑም በተጨማሪ ስራ ላይ የነበራቸውን አቅም እንዲያጡ ማድረጉን ይናገራሉ።
በህመሙ ከመያዛቸው በፊት አቅማቸውን አሟጠው እንደሚሰሩ የተናገሩት አቶ ዳዊት አሁን በሚሰማቸው የድካም ስሜት ምክንያት በማህበራዊ ህይወታቸው እንደፈለጉ እንዳይሳተፉ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።
መድሀኒቱን በየሳምንቱ እየገዙ የሚጠቀሙ ቢሆንም በተፈለገው ግዜ በፋርማሲዎች የማይገኝ በመሆኑ መድሃኒት ፍለጋ ብዙ ርቆ ለመሄድ እንደሚገደዱ ገልጸው፤ መድሃኒቱ ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥም እንደሆኑ ነው ያሳወቁት።
የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም ሙሳ እንዳሉት ማህበሩ ለህጻናት የኢንሱሊንና ሌሎች ድጋፎች እያደረገ ሲሆን ለአዋቂዎችም የተለያዩ ተጓዳኝ ምርመራና ግንዛቤ እየፈጠረ ይገኛል።
ማህበሩ በሀገሪቱ በሚገኙ ሰላሳ በሚደርሱ የህክምና ተቋማት ኢንሱሊንና ሌሎች የስኳር ህመም መድሀኒቶች ለህጻናት በማቅረብ ህክምናውን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ራሳቸውን ችለው መርፌውን እንዲወጉ የሚያስችል ስልጠና ለስኳርታማሚ ህጻናት እየተሰጠ ይገኛል ያሉት የማኅበሩ ስራአስኪያጅ በቀጣይ ለአዋቂ ህመምተኞችም ኢንሱሊን በነጻ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ የስኳርና ሆርሞን ችግሮች ስፔሽሊስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ እንደሚሉት የስኳር ህመም እድሜን ሳይለይ ስርጭቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው።
በፓውሎስ ሆስፒታል አምስት ሺ የሚደርስ የስኳር ህመምተኛ ታካሚ እንዳለና በአመት አስከ አስራሁለት ሺ የሚደርሱ ክትትሎችንእንደሚደረግ ተናግረዋል።
የታማሚ ቁጥር መብዛት በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ሲሳይ ከቁጥሩ አንጻር አንድ ህመምተኛ በአምስት ወር አንዴ ክትትል እንዲያደርግ ለመቅጠር ተገደናል ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ በቂ የመድሀኒት አቅርቦት ቢኖርም አንድ ሰው ለክትትል ወደ ሆስፒታሉ ስሄድ የአምሰት ወር መድሀኒት ይዞ የሚሄድበት ሆኔታበመኖሩ በሌላ ወቅት የሚመጣ ታካሚ መድሀኒት የሚያጣበት ሆኔታ እንደሚከሰትም አስረድተዋል፡፡
በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የስኳር ህመም ስርጭት ፈጣን መፍትሄ ይፈልጋል የሚሉት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስኳር ህመም ሐኪም ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ ፤ተጋላጭነቱን ለመቀነስም ህብረተሰቡ የአኗኗርና የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።