በፓርኩ የተከሰተው እሳት ከ60 ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት አወደመ - ኢዜአ አማርኛ
በፓርኩ የተከሰተው እሳት ከ60 ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት አወደመ
ጎንደር መጋቢት 21/2011በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከ60 ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት ማውደሙን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
እሳቱን ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት እሜት ጎጎና ሳንቃ በር በተባሉ የፓርኩ አካባቢዎች ባለፈው ሐሙስ ምሽት የተከሰተው እሳት የጓሳ ሳርና ቁጥቋጦ አውድሟል፡፡
እሳቱ አሁን ላይ በፍጥነት ከመስፋፋት የተገታ ቢሆንም፤ የአካባቢው የተፈጥሮ አቀማመጥ የቁጥጥር ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
ቃጠሎውን በመቆጣጠር ሂደት የደባርቅ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ የቱሪስት ማህበራት አባላት፣ የጎንደርና የደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች እንዲሁም የጎንደር ከተማ ወጣቶችና የአካባቢው የጸጥታ ኃይል እየተረባረቡ ነው፡፡
ቃጠሎው ወደ ሌሎች የፓርኩ አካባቢዎች እንዳይዛመት ለማድረግም የእሳት መከላከያ ጉድጓዶችና እርከኖች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ቃጠሎው የተነሳው በአብዛኛው ዋልያና ቀይ ቀበሮ በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ባለመሆኑ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አቶ አበባው አስታውቀዋል።
በፓርኩ ሌሎች የዱር እንስሳት ላይም የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል፡፡
የቃጠሎው መነሻ በውል አልታወቀም የሚሉት ኃላፊው፣ሆኖም ቀደም ባሉት ዓመታት በፓርኩ የሚነሳው እሳት በእርሻ መሬት ምንጣሮና በማር ቆረጣ ወቅት በሚፈጠር እሳት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የፓርኩን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል የሕግ አካላት ሕገ-ወጥ ተግባራትን ፈጽመው ለሕግ በሚቀርቡ ግለሰቦች ላይ የሚያሳልፉት ቅጣት አናሳ መሆን ፓርኩን ለአደጋ እያጋለጠው እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ፓርኩን በየዓመቱ ከሚከሰተው የእሳት ቃጠሎ ለመታደግ በዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ ተሸከርካሪዎችና የሰለጠኑ ባለሙያዎች መሟላት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡
ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ መገኛ መሆኑ ይታወቃል።