ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል 3 ዞኖች ጊዜያዊ የሠላምና ጸጥታ ኮሚቴ ተቋቋመ

ሚዛን መጋቢት 20/2011 በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ፣ካፋና ሸካ ዞኖች አለመረጋጋትን  ለማስቆም ጊዜያዊ የሠላምና ጸጥታ  ኮሚቴ መቋቋሙን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ አስታወቀ።

ከየዞኖቹ መስተዳድር አካላትና የጸጥታ መዋቅር ጋርም ዛሬ በሚዛን ከተማ ውይይት ተደርጓል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል እንደገለጹት  ባለፉት ስምንት  ወራት በአካባቢው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስና የመኖር ህልውና ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።

በእነዚህ ጊዜያት  በነበረው ግጭትም የሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳትም መድረሱን አመልክተው የዜጎች መፈናቀልና ንብረት መውደሙንም  ተናግረዋል፡፡

የጸጥታ ችግሩ አሁንም  በመኖሩ ዜጎችን ከጉዳት ለመጠበቅና አካባቢው ቀድሞ ወደነበረበት መረጋጋት  ለመመለስ የሠላምና ጸጥታ ኮሚቴ ሊቋቋም እንደቻለ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ አስታውቀዋል።

የኮሚቴው አባላት ከዕዙ ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ፣የደቡብ  ክልል ልዩ ኃይል ፣ ከዞን አስተዳደርና ከሌሎችም የጸጥታ አካላት የተወጣጡ ናቸው፡፡

ዓላማውም በህብረተሰቡ ላይ እደረሰ ያለውን ጉዳትና በደል በማስቆሞ ተረጋግቶ የመኖርና ተንቀሳቅሶ የመስራት መብትን ማረጋገጥና  ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን ለህግ ማቅረብ ነው።

እንደ ብርጋዴል ጀኔራል አሰፋ ገለጻ ከሸካ ዞን ቴፒ ከተማና  የኪ ወረዳ ፣ ከቤንች ማጂ  ጉራፋርዳ ፣ሱርማ ፣ቤሮ እና  ማጂ፣ መኤኒት ጎልዲያ እና መኤኒት ሻሻ ወረዳዎች ከካፋ ዞን ደግሞ ዴቻና ጎባ ወረዳዎች የችግሩ ዋና ዋና ማዕከላት እንደሆኑ ተለይተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎችም ማንኛውም ነዋሪ  ጉዳት የሚያደርሱ ስለታማ ዕቃዎችን ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከደቡብ ሱዳን የሚያዋስኑና በድንበር አካባቢዎች ጉምሩክን ጨምሮ ጥብቅ የፍተሻ  ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

በአከባቢው  የህገወጥ መሳሪያ ዝውውርና የተደራጀል  ወንጀል የሚፈጽሙ ቡድኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የምዕራብ ዕዝ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል መብራቱ ኃይሉ በበኩላቸው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመቆጣጠር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ግጭቶችን ማስቆም የሰላም ኮሚቴው  ተልዕኮ  መሆኑን ተናግረዋል።

ጊዜያዊ የሠላምና ጸጥታ ኮሚቴው ለአንድ ወር የሚቆይ መሆኑን አመለክተው በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ከየዞኖቹ አስተዳደር አካላትና ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የመመለስ ስራም ይከናወናል ተብሏል።

ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥና ወደቀድሞ መረጋጋት እንዲመለስ  የሁሉንም ጥረት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ  የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ናቸው ።

"የአካባቢው ሰላም እንዲመለስ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል "ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም