አውሮፕላን ውስጥ መንትያ ልጆች የተገላገለችው ኢትዮጵያዊት አዲስ አበባ ገባች - ኢዜአ አማርኛ
አውሮፕላን ውስጥ መንትያ ልጆች የተገላገለችው ኢትዮጵያዊት አዲስ አበባ ገባች

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 ከጅዳ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ በነበረ የሳውዲ ዓረቢያ አውሮፕላን ተሳፍራ እዛው አውሮፕላኑ ውስጥ መንታ ሴት ህፃናት በመውለዷ አስመራ ዓለምቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እንድታርፍ የተደረገችው ኢትዮጵያዊት እናት ዛሬ አዲስ አበባ ገባች።
በሥራ ምክንያት ሳዑዲ አረቢያ መዲና ከተማ የምትኖረው የ35 ዓመቷ ወይዘሮ ጀነት ሁሴን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር በመሆኗ አገር ቤት ለመዉለድ ነበር ባለፈው መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓም በሳዑዲ አየር መንገድ የተሳፈረቸው።
ሆኖም እርሷ ያሰበችው ሳይሆን ቀረና ከጊዜዋ ቀድማ መንትያ ሴት ልጆቿን መንገድ ላይ ተገላግላለች።
ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው-
አውሮፕላኑ በኤርትራ አየር ክልል ውስጥ እንደገባ ነበር ወይዘሮ ጀነት በድንገት ምጥ የያዛት።
እናም ፖይለቱ ከኤርትራ አየር ተቆጣጣሪዎች ጋር በመነጋገር አውሮፕላኑ አስመራ አየር ማረፊያ እንዲያርፍ ተደረገ።
አንዷ ህፃን ወደዚህ ምድር የተቀላቀለችው አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሲሆን ሁለተኛዋ ግን አውሮፕላኑ እንዳረፈ ነበር የተወለደቸው።
መንታ ልጆቿን ይዛ ዛሬ አዲስ አበባ የገባችው ወይዘሮ ጀነት ለጋዜጠኞች በሰጠችው ቃል አውሮፕላን ውስጥ ከተሳፈረች በኋላ ባልጠበቀችው ሁኔታ ምጥ እንደጀመራት ነው የገለጸችው።

ኤርትራውያን ሃኪሞች ለእናትየውና መንታ ህፃናቱ አስፈላጊውን እርዳታ አድርገውላቸዋል። ለተጨማሪ እንክብካቤም ኦሮታ ሪፈራል ሆስፒታል ወስደዋቸዋል።
ወይዘሮ ጀነት እንደገለጸችው አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ አስመራ መሆኗን ስታውቅ ስጋት ተሰምቷት ነበር።
ሆኖም በአስመራ በኤርትራውያን የጤና ባለሙያዎች ፈጽሞ ያልጠበቀችው እንክብካቤና የህክምና ድጋፍ እንደተደረገላት ገልጻለች።
ለመንትያ ልጆቿም አስመራ እና ሀያት የሚል ስም እንዳወጣችላቸው ተናግራለች።
ህጻናቱ ከጊዜያቸው ቀድመው በስምንት ወር የተወለዱ እንደመሆናቸው መጠን በማሞቂያ ክፍል ውስጥ ሆነው አስፈላጊው የህክምና ክትትል ተደርጎላቸዋል።
በአስመራ የልጆቹንና የራሷን ጤንነት ስትከታተል ቆይታ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የገባችው ወይዘሮ ጀነት በመቀጠልም ቤተሰቦቿ ወደሚገኙበት ደሴ ከተማ ታመራለች።
ለጀነቲ ሁሴንና ለመንትያ ሴት ልጆቿ ለተደረገላቸው እንክብካቤ ለሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ለሀገረ ኤርትራ ህዝብና መንግስት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርቧል።
ማንኛውም ጤነኛ እርግዝና ያላት ሴት እስከ 27ኛ የእርግዝና ሳምንት ድረስ በአውሮፕላን ጉዞ ብታደርግ የሚያስከትለው የጤና ችግር እንደማይኖር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህም ሆኖ ግን ነፍሰ ጡር ሴት በረራ ከማድረጓ በፊት ከሃኪም ጋር መመካከር ያስፈልጋታል።
ከ27ኛ የእርግዝና ሳምንት በኋላ የሚደረግ የአውሮፕላን ጉዞ ለጤና አስጊ ሲሆን ከ36ኛ ሳምንት በኋላ የሚደረግ ጉዞ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።