በኢትዮጵያ ከእንስሳት ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከእንስሳት ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 በኢትዮጵያ ከእንስሳት ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮግራም በዓለም ዓቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲቲዩት ይፋ ሆነ።
የእንስሳትን ጤንነት በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችለው ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አማካይነት የሚተገበር ነው።
የእንስሳትን ጤና በመጠበቅ ለገጠር ልማት ወይም (HEARD) የሚለው ፕሮጀክት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2019 እስከ 2022 የሚቆይ ሲሆን በኢትዮጵያ በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።
የፕሮጀክቱ ዓላማም እንስሳት በበሽታ እንዳይጠቁ፣ የክትባት አገልግሎት በጥራትም ሆነ በብዛት መጨመር፣ የእንስሳት በሽታን የመከላከል አቅም ማሳደግ እና በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው የእንስሳት በሽታን በዘላቂነት መከላከል መሆኑን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ብርሃኑ ታዬ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የያዘው ፕሮጀክት ከአውሮፓ ህብረት፣ ከዓለም ምግብ ድርጅትና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው።
በተለይ የእንስሳት አርቢዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት እና ገቢያቸው የሚሻሻልበት መሆኑን ተወካዩ ጠቁመዋል።
ከእንስሳት የሚገኘውን ምርት በጥራትና በብዛት በመጨመር እንዲሁም የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ 15 ሚሊዮን ዩሮ የተያዘለት ሲሆን ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ኃብት ቢኖራትም ከዘርፉ በሚፈለገው መጠን እየተጠቀመች አለመሆኑ ይነገራል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ባለሙያና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር መላኩ አሰፋ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ፕሮጀክቱ ስራ ላይ ሲውል "ከእንስሳት የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት" ያሳድጋል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት በአማራ፣ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሚጀመር ሲሆን በቀጣይ በግብርና ሚኒስትር አማካይነት በአገር አቀፍ ደረጃ በሌሎች አካባቢዎችም ይተገበራል ተብሏል።
የእንስሳት ጤናን ማሻሻል፣ የባለሙያዎችና የእንስሳት ጤና ተቋማትን አቅም ማጎልበትና የምግብ ጤንነትን በመጠበቅ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን በመከላከል ላይም የፕሮጀክቱ ትኩረት ይሆናል።
የአርብቶ አደሩንና አርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥም እገዛ እንደሚኖረው ዶክተር መላኩ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ የእንስሳት ሐኪሞች ማህበር የተወከሉትና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ፋሲል አወል በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በመንግስትም ሆነ በግል በእንስሳት ጤና ተቋማት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅም የሚያጎልብት ነው ብለዋል።
በግል የሚሰሩ የእንስሳት ሐኪሞች እንዲጠናከሩም የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።