ፖሊስ በእነ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 41 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አልቻልኩም አለ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ በእነ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 41 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አልቻልኩም አለ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 ፖሊስ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር የክስ መዝገብ የተከሰሱ 41 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አልቻልኩም አለ።
ፖሊስ በአቶ አብዲ መሐመዱ ዑመር የክስ መዝገብ ከተከሰሱ 47 ተጠርጣሪዎች መካከል እስካሁን በቁጥጥር ስር ያዋለው 6ቱን ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳልቻለ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በ47 የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ተከሳሾቹ ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በፈጠሩት ግጭቶች የ59 ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግስት ተቋማት፣ የግለሰቦች ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ተቋማት ተቃጥለው እንዲወድሙ በማድረግ ከ412 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ህግ አስረድቷል።
በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች ከአካባቢው ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረጋቸውንም የክስ መዝገቡ ያመለክታል።
ፖሊስ በእነ አብዲ መሐመድ ዑመር የክስ መዝገብ የተከሰሱ 41 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንዳልቻለ ዛሬ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ገልጿል።
ዓቃቤ ህግ በበኩሉ ቀሪ ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር በማዋል በኩል ፖሊስ በአግባቡ እየሰራ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው ገልፆ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል።
ፖሊስ በበኩሉ ከክልሉ ስፋት አንፃር በፍጥነት ተከሳሾቹን ካሉበት ፈልጎ በቁጥጥር ስር ለማዋል አዳጋች እንደሆነበት አስረድቷል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩለቸው ፖሊስ ተከሳሾችን ለመያዝ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም በእስር ላይ ያሉትን ሰዎች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት ይጋፋል ሲሉ ተከራክረዋል።
በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች የፍርድ ሂደት እንዲጀመር ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጣቸውም ጠበቆቹ ጠይቀዋል።
ፖሊስ ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እያከናወነ ያለው ስራ አድካሚና ውስብስብ መሆኑን እንገነዘባለን ያለው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ፈልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፖሊስ ተከሳሾቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገው ክትትል ካልተሳካ ተከሳሾቹ ከሚኖሩበት አካባቢ ከሚመለከተው አካል አለመኖራቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በቀጠሮ ቀን ይዞ እንዲቀርብም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።