በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እርካታ ቀንሷል - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እርካታ ቀንሷል
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በታካሚዎች ዘንድ ያለው እርካታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ።
የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት "የሆስፒታሎች የአገልግሎት ጥራት እና የታካሚዎች እርካታ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት ዛሬ ተካሄዷል።
የኢንስቲትዩቱ የጥናት ቡድን በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ 11 ሪፈራል ሆስፒታሎች እና 450 ታካሚዎች ላይ ጥናት አካሂዷል።
ጥናት ከተካሄደባቸው ታካሚዎች ውስጥ 51 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ 49 በመቶ ደግሞ ወንዶች ናቸው።
በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የቢዝነስ ልማትና የሙያ ፈቃድ ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ አማረ ጅማ እንደገለጹት፤ ታካሚዎች በህክምና ተቋማት ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃት ያላቸው እርካታ 66 ነጥብ 5 በመቶ ነው።
በተቀመጡት የእርካታ መለኪያ መስፈርቶች ውስጥ እንክብካቤ፣ አክብሮት፣ ትህትና፣ ትብብር፣ እምነት፣ ቀረቤታና ትስስር ላይ ታካሚዎች ያላቸው የእርካታ መጠን 62 ነጥብ 96 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ የታካሚዎች የእርካታ መጠን ከዚህ በፊት በመንግስት ሆስፒታሎች ላይ ከተጠኑ ጥናቶች ጋር ሲነጻጸር የእርካታ መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ ጥናቶች የነበረው የእርካታ መጠን ከ70 እስከ 90 በመቶ ይደርስ እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሩ ''በአሁኑ ወቅት የተካሄደ ጥናት ግን የእርካታ መጠኑ መቀነሱን በግልጽ የሚያሳይ ነው'' ብለዋል።
ታካሚዎች ለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፣ ለታካሚዎች የሚሰጠው አክብሮት አናሳ መሆን፣ ታካሚዎችን በቅንነት አለማስተናገድ እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ከታካሚዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ደካማ እንደሆነ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል።
በሆስፒታሎቹ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ማነስ፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓት አለመኖር፣ በታካሚዎችና በህክምና ባለሙያዎች መካከል ያለው ቀረቤታ የላላ መሆን፣ በህክምና ባለሙያዎች ላይ አመኔታ ማጣትና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ በሚፈለገው ደረጃ አለመኖር ሌሎች የጥናቱ ግኝቶች ናቸው።
በሆስፒታሎች ትርጉም ያለው የቅሬታ አቀራረብ ስርአት መዘርጋት፣ ታካሚዎችን አክብሮ መስራት፣ በጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዘውን ሩህሩህ፣ አክባሪና ተንከባካቢ የጤና ባለሙያ ማፍራት ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በጥናቱ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ናቸው።
የውስጥ ሰራተኞችን እርካታ ማሻሻል፣ የፋይል አያያዝን ማዘመን፣ የታካሚና የህክምና ባለሙያ ትስስስርን የተመለከቱ ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ዓለም አቀፍ የጥራት ተሞክሮዎችን መውሰድና ሆስፒታሎች ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ ማድረግ ሌሎች ምክረ ሀሳቦች ናቸው።
የተለያዩ ሆስፒታሎች የስራ ኃላፊዎች በጥናቱ ላይ በሰጡት አስተያያት ጥናቱ የእርካታ መለኪያ የሆነውን የታካሚዎችና የህክምና ባለሙያዎች ግንኙነትና ቀረቤታ የጥናቱ ዋንኛ አላማ መሆኑ በመልካምነት እንደሚነሳ ገልጸዋል።
ጥናቱ ለናሙና የወሰዳቸው ታካሚዎችን ቁጥር ቢጨመር አጠቃላይ ግምት ሲሰጥ ተአማኒ እንዲኖረው ያደርግ ነበር የተመረጡት ሆስፒታሎች አብዛኞች በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው ነገር ግን አብዛኛው ህዝብ የሚታከመው በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ የእርካታ መጠን ቀንሷል የሚለው ነገር ነባራዊውን እውነታ የሚያሳይ ነው ወይ? በሚል የሆስፒታሎች የስራ ሃላፊዎች ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢኒስቲትዩት የቢዝነስ ልማትና የሙያ ፈቃድ ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ አማረ ጅማ የእርካታ መለኪያ መስፈርቶቹና ናሙናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙና የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው እንደሆኑ አመልክተዋል።
የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው የእርካታ መጠን መቀነሱን መሆኑንና በቀጣይ በሚደረጉ ጥናቶች የሆስፒታሎችን ቁጥር በማሳደግና ሌሎች የእርካታ መለኪያ መስፈርቶችን አካቶ የተሻለ ገላጭ የሆነ ነገር ማግኘት እንደሚቻልም አስረድተዋል።