የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ባለማግኘታችን ተቸግረናል - የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ባለማግኘታችን ተቸግረናል - የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች
ደብረ ማርቆስ ግንቦት 24/2010 በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር የቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ማህበር መስርተው ቢንቀሳቀሱም ጥያቄያቸው ተገቢ ምላሽ ባለማግኘቱ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የቀበሌ 05 ነዋሪ ተመላሽ የሰራዊት አባል መቶ አለቃ ታደለ ሙሉነህ እንደገለጹት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ማህበር ከመሰረቱ አንድ ዓመት ተኩል ሆኗቸዋል። አባላቱ የሚጠበቅባቸውን የቁጠባና ለመሬት ካሳ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ቢያዘጋጁም እስካሁን ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለተመላሽ የሰራዊት አባላት በተደራጁ ከ3 እስከ 5 ወራት በልዩ ሁኔታ ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው ''እኛ ግን ጥያቄያችን ለረጅም ጊዜ መልስ ሳያገኝ እየተጉላላን ነው'' ብለዋል፡፡ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ የቤት ኪራይ ለመክፈል እና ልጅ ለማሳደግ መቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ የአደይ አበባ የቤት ስራ ማህበር ሊቀመንበርና የቀበሌ 07 ነዋሪ ቴዎድሮስ ዘውዴ ናቸው። ወደ ከንቲባና ቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ጥያቄ ሲያቀርቡም 'ቦታ የሚለካ የባለሙያ ዕጥረት በመኖሩና ካሳ የሚገምት ኮሚቴ ባለመቋቋሙ ነው' በሚል ምክንያት ጥያቄያችን እስካሁን ምላሽ ያላገኘው። የቀበሌ 05 ነዋሪና የዳር ድንበር በክብር ተመላሽ የቤት ስር ማህበር ሊቀመንበር አስር አለቃ የማነ ብርሃን በበኩላቸው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ለማግኘት የማህበሩ አባላት ከ260 ሺህ ብር በላይ መቆጠባቸውን ተናግረዋል። ''የቤት መስሪያ ቦታ ባለማግኘታችን ከተለያዩ የገንዘብ ቁጠባ ተቋማት ተበድረን ያስያዝነው ብር ያለአግባብ ወለድ እየቆጠረብን ነው'' ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዝግአለ ካሳ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት የተደራጁ ተመላሽ የሰራዊት አባላትም ሆነ ነዋሪዎች ቦታ ያልተሰጠው የባለሙያ እጥረት በማጋጠሙ ነው። ጽህፈት ቤቱ ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ከሌላ መስሪያ ቤት ባለሙያ በትውስት በማስመጣት ወደስራ አንዲገባ መደረጉን ጠቅሰው የቦታ ሽንሸናውና የመሬት ካሳ ክፍያው እንደተጠናቀቀ ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝ ገልፀዋል፡፡ የተመላሽ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ የሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን የቦታ ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ናቸው። የቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ያዘጋጀውን የቦታው ካሳ ክፍያ ለመገመት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የካሳ ግምት ጥናቱና ክፍያው እንደተጠናቀቀ ቦታውን እስከቀጣዩ ወር መጨረሻ ለአባላቱ እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል፡፡