ቀጥታ፡

የቦይንግ ኩባንያ ከኢትዮጵያው አየር መንገድ የአውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ ክስ ተመሰረተበት

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 የቦይንግ ኩባንያ ከኢትዮጵያው አየር መንገድ የአውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ  ክስ ተመሰረተበት።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወሳል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች በሙሉ ህይወት አልፏል።

ከሟቾቹ መካከል የሩዋንዳዊው ጃክሰን ሙሶኒ ቤተሰቦች በአሜሪካሪ ቺካጎ ከተማ በሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት በኩባንያው ላይ ክስ መሰርተዋል። ሩዋንዳዊያኑ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን የአውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ላይ የዲዛይን ችግር እንዳለበት በመግለፅ ነው ክሱን የመሰረቱት።

የቦይንግ ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ በኋላ በቀረበበት የመጀመሪያ በሆነው ይሀን ክስ በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡን የእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን በደረ ገጹ አስፍሯል።

ከትናንት በስቲያ ቦይንግ ከአደጋዎቹ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው በአውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ላይ ያለው ችግር መፍትሄ እንዳገኘ መግለጹ ይታወሳል።

የአደጋው መርማሪዎች በአሁኑ ሰአት በፈረንሳይ የአደጋው ምክንያት ምን እንደሆነ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም