ቀጥታ፡

“ወደ ኃላፊነት ስመጣ የደሞዝ ጥያቄ መመለስ የማይችል ኢኮኖሚ ነው የተቀበልኩት”- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 "ወደ ኃላፊነት ስመጣ የደሞዝ ጥያቄ መመለስ የማይችል ኢኮኖሚ  ነው የተቀበልኩት" ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት  በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢንቨስትመንትና ትንንሽ ድጋፎችን ሳይጨምር ሶስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ እሳቸው ወደ መንበረ ስልጣን ሲመጡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት በአስከፊ አረንቋ ውስጥ ወድቆ ነበር።

ኃላፊነትን በተቀበሉ በሳምንቱ የቀረበላቸውን የ20 ቢሊዮን ብር የደሞዝ ጥያቄ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት  መመለስ እንዳልቻለ በመጠቆም፤

ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ቆሞ አገሪቱን ለተጨማሪ የሃብት ብክነት ሰለባ አድርገዋት እንደነበር ነው ዶክተር ዓብይ ያብራሩት።

ችግሩን ለማስተካካል መንግስት ባከናወናቸው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ተግባራት ኢንቨስትመንትንና ትናንሽ ብድሮችን ሳይጨምር ሶስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወለዱ ከፍተኛ የሆነና በአጭር ጊዜ የሚከፈል ብድር ከቻይና መውሰዷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "የእነዚህ ብድሮች የመክፍያ ጊዜያቸው በዚህ ዓመት ነበር" ብለዋል።

ከቻይና ጋር በተሰረው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መክፈል የሚገባንን ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ  ብድር እንዲራዘምልን አድርገናል ነው ያሉት።

ኢትዮጰያ ዋነኛ የስትራቴጂክ አጋር ከሆነቻት ቻይና ጋር ያላትን ወዳጅነት አሁንም አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም