የፕሪሚየር ሊጉ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።
ነገ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ደደቢት ከደቡብ ፖሊስ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
ከነገ በስቲያ በሳምንቱ መርሃ ግብር ሰባት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከስሑል ሽረ፣በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና፣በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።
በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከኢትዮጵያ ቡና እና በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።
የእሁድ ሁሉም ጨዋታዎች ዘጠኝ ሰአት ነው የሚደረጉት።
በ19ኛ ሳምንት መከላከያ ከደደቢት መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም በ10 ሰአት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ በ10 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ የመርሃ ግብር ለውጥ ተደርጓል።
በተመሳሳይ በ19ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም 10 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ በ10 ሰአት ይካሄዳል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ39 ነጥብ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ31 ነጥብ ሁለተኛ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 29 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
መከላከያ፣ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል እና የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።