የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2011"የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይኑረው ሲባል ክልሉ ለከተማዋ በሚያቀርበው ግብዓት ልክ ተጠቃሚ ይሁን ማለት እንጂ ሌላ የተለየ ትርጉም የለውም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ።
ልዩ ጥቅሙ በአዲስ አበባ የሚኖር ኦሮሞ ከሌላው ኗሪ በተለየ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ተደርጎ የሚናፈሰው መረጃ የተሳሳተ መሆኑንም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
በዚሁ መግለጫቸውም አዲስ አበባ ለህንጻዎቿ የሚሆኑ ግብዓቶችን እንዲሁም የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከአጎራባቿ የኦሮሚያ ክልል ታገኛለች ሲሉ ገልፀዋል።
በእነዚህ ክልልች የሚኖሩ ዜጎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንደሌላቸው ጠቁመው ፤ ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምታደርገው መስፋፋት በዙሪያዋ የሚገኙ 170 ሺህ ቤተሰቦች ተፈናቅለዋል ብለዋል።
የእነዚህ ዜጎችን መብት ለኦሮሞ ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጰያዊ ጉዳይ መሆን እንዳለበትም አሳሰበዋል።
ይሄን አርሶ አደር ባልተገባ ሁኔታ መብቱን እንዳይጣስ መታገል ከኦሮሞዎች ብቻ የሚጠበቅ አይደለም።የትኛውም ኢትዮጵያዊ ሄዶ አጥንቶ ያልተገባ ነገር ከተደረገ እኩል መቆም ይኖርበታል።እንደዚያ ከሆነ ነው የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ የምንገነባው።አሁን ከዚህ አካባቢ 170 ሺህ ቤተሰብ ተፈናቅሏል።ማጥናት የእነሱን ሁኔታ ማስተካከል ከሁላቸንም ይጠበቃል።”
ከዚህ አንጻር የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይኑረው ሲባል ከተጠቀሰው ሁኔታና ክልሉ ከሚያቀርበው ግብዓት አንጻር የሚገባውን ይጠቀም ማለት እንደሆነ አብራርተዋል።
ጉዳዩን በአዲስ አበባ የኦሮሞ ተወላጆች ልዩ ጥቅም አድርጎ በተሳሳተ መንገድ የሚረዱ አካላት እንዳሉም አውስተዋል።
አዲስ አበባ የሚኖሩ ዜጎች ጉዳዩን በሚመለከት በሚናፈሰው የተሳሳተ ስጋት እንዳደረባቸው መገንዘባቸውንም አክለዋል
“የኦሮሞ ህዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው አዲስ አበባ የሚኖሩ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ በተዛባ መረጃ ሌሎች ወንድሞቻችን አደጋ ሊያደርሱብን ነው የሚል ሰጋት እየፈጠረባቸው ነው።ይሄ ትክክል አይደለም፤አንደኛው ለአንዳችን ጋሻ እንጂ ስጋት መሆን የለብንም።” ነው ያሉት፡፡