ቀጥታ፡

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

ጎንደር መጋቢት 20/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከትናንት ጀምሮ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሳት ቃጠሎው የተከሰተው በፓርኩ ሁለት አካባቢዎች ነው፡፡

በተለይ እሜት ጎጎ በተባለው አካባቢ የተነሳው ቃጠሎ ግን ከቦታው ገደላማነት የተነሳ  እሳቱን ለመቆጣጠር እንዳልተቻለ  አስረድተዋል፡፡

ቃጠሎው በጓሳ፣ ሳርና የቁጥቋጦ ዛፎች ላይ መከሰቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የቃጠሎው መንስዔ ለጊዜው አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃም በፓርኩ የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡

ነገር ግን ሳንቃ በር በተባለው የፓርኩ አካባቢ የተነሳው ቃጠሎ በኅብረተሰቡና በስካውቶች ርብብርብ በቁጥጥር ሥር ውሏል ብለዋል፡፡

በፓርኩ ባለፈው ዓመትም ቃጠሎ ደርሶ ነበር፡፡

ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ ያሉት በዚሁ ፓርክ ነው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም