ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ 13 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተሰማሩ 38 ኩባንያዎች ጋር በመስራቱ 13 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን እንደቻለ ገለጸ። ኢንስቲትዩቱ  በአገሪቷ የተጀመረውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርታማነትና  ጥራትን አስጠብቆ ለማስቀጠል ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ጋር እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሀገር አቀፍ የካይዘን ንቅናቄ መፍጠሪያ መድረክ እና አምስተኛው ዙር የጋራ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ  በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በአገራችን የሚጠበቀውን የኢንዱስትሪ የስራ ባህል ለማሻሻልና የዘርፉን ባለቤትነት ለማረጋገጥ  ማንፋክቸሪንግን ማዕከል አድርጎ እየተሰራ ነው። እንደ አቶ መኮንን ገለጻ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተሰማርተው እየሰሩ ካሉ 38 ኩባንያዎች በበጀት አመቱ የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ ለማድረግ በመሰራቱ 13 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብትን ከብክነት ማዳን ተችሏል። ተቋማቱ በስራ አካባቢያቸው የሚገኙት ብክነቶች በመቀነስና በዘላቂነት ደግሞ በማስወገድ ሀብትን ከብክነት በማዳን ውስን ሀብትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተጠቅሞ ተወዳዳሪ ለመሆን ያሉባቸውን ችግች መፍታት እንዳለባቸው ነው የገለጹት። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር  ዴኤታው አቶ አያና ዘውዴ በበኩላቸው የካይዘን የስራ አመራር  ፍልስፍና ለአገራችን አስፈላጊነቱ ከፍተኛ  ነው ብለዋል። የተጀመረውን  የዘርፉን እድገት እና ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነው፤ ይህም ሌሎች አገራት በተለይም በኢሲያ ያሉ አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት የወጡበት ስልት በመሆኑ በእኛም አገር ትግበራው በተጀመረበት አጭር ጊዜ የሚታይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት። ከኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ጋር እየሰሩ የሚገኙ 38 ኩባንያዎች በፊት በአማካይ 40 በመቶ ነባራዊ የስራ አተገባበር የነበራቸው ሲሆን  ከኢስቲትዩቱ ጋር መስራት ከጀመሩ በኋላ ግን 76 በመቶ የስራ አተገባበር መፍጠራቸውም ተገልጿል። በኢንስቲትዩቱ በኩል ዘርፉን በሙያዊ የማማከር ስራ ለመደገፍ 6ሺ 249 አመራሮችና የፊት መስመር ሰራተኞች ስልጠና ወስደው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 54 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል። በአጠቃላይ ወደ ተግባር ከገቡት ኩባንያዎች ውስጥም 71 በመቶ ያህሎቹ በጥሩ ለውጥ ላይ ያሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ተጠቁሟል። በዘርፉ ከተካተቱት ውስጥም፣ የምግብና የመጠጥ ኩባንያዎች፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች፣ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች እና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል። ኩባንያዎቹ የተረጡበት መስፈርትም የኤክስፖርት ምርት ላይ የተሰማሩና ከፍተኛ የብክነት ችግር ያለባቸው እንዲሁም ከፍተኛ የሰው ኃይል ያላቸው መሆኑ ተጠቁሟል። የካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዓላማ ከፍተኛ የስራ ጥበብ ፍልስፍናን በተቋማትና በስራ ቦታ ማስረፅ ሲሆን፤ ምቹ የስራ ቦታን በመፍጠር ሀብትን ከብክነት ማዳንም ግቡ ነው። ይህ የስራ ፍልስፍና የተጀመረው እ.አ.አ 1940ዎቹ መባቻ ላይ በጃፓን አገር ነበር ። በአገራችንም ተግባራዊ መሆን ከጀመረ 6 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ የኢሲያ አገራትን ጨምሮ በምዕራብ አውሮፓና በሌሎችም የዓለም አገራት እየተሰራበት ያለ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም