ቀጥታ፡

በዜጎች መፈናቀልና ሞት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 ባለፈው አንድ ዓመት በዜጎች መፈናቀልና ሞት ምክንያት ከአንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

መንግስት ከዚህ በፊት እንደተለመደው ተጠርጣሪዎችን በግፍ ስለማያስር የህግ የበላይነት ያልተከበረ የሚመስላቸው አካላት እንዳሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በጅግጅጋ፣ ሐዋሳ፣ ቡራዩ፣ ወለጋ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች ዜጎችን በማፈናቀልና ሰብዓዊነት በጎደለው አካሄድ በመግደል የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ 50 በላይ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር ይገኛሉ።

''ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በጅግጅጋ 47፣ በቡራዩ 108፣ በአዲስ አበባ 68፣ በወለጋ 200፣ ከጌዲዮ ህዝቦች መፈናቀል ጋር በተያያዘ 300፣ በሐዋሳ 100 እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ 224 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል'' ነው ያሉት።

በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ኢ-ሰብዓዊነት በተሞላበት ጭካኔ ሰው ዘቅዝቀው የሰቀሉ ጥፋተኞች ላይ በሁለቱ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደም ገልጸዋል።

ይህም መንግስት የህግ ጥሰት ላይ ያለውን አቋም እንደሚያሳይ ነው ያብራሩት።

የህግ የበላይነት አለመከበር በአገር ላይ የሚያመጣውን ቀውስ መንግስት በግልጽ እንደሚረዳም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

መንግስት ህግን በማስከበር ሰበብ ዜጎችን በጅምላ የማሰር ፍላጎት እንደሌለው ተናግረው፤ ''ይህ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የሰፈነ የማይመስላቸው አካላት አሉ'' ብለዋል።

መንግስት የህግ ጥሰቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም