ከተማ አስተዳደሩ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት የብድር አሰጣጥ ማሻሻያዎች አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት የብድር አሰጣጥ ማሻሻያዎች አደረገ
አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት የብድር አሰጣጥ ማሻሻያዎች ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይፋ አደረገ።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ከክፍለ ከተሞች የስራ ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በስራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸም ላይ ምክክር አድርገዋል።
በመድረኩ በቀረበው የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደተመለከተው በበጀት ዓመቱ ከ161 ሺህ በላይ የመዲናዋ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወነው ለ66 ሺህ 200 ወጣቶች ብቻ ነው።
ከ79 ሺህ በላይ የስራ እድል አማራጮች የተለዩ ቢሆንም ወደ ተግባር የተለወጡት 15 ሺህ የስራ ዕድሎች ብቻ መሆናቸውም ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ 20 በመቶው ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸውን የገለጹት ኢንጂነር ታከለ ዑማ፤ ለወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት የአስተዳደሩ ካቢኔ ሁለት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ማጽደቁን አስታውሰዋል።
አዲስ አበባ የትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ማዕከል ሳይሆን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቴክኖሎጂ፣ አገልግሎትና ቱሪዝም ከተማ መሆን እንዳለባት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ማነቆ የሆኑ ህግጋትና አሰራሮች እንደሚስተካከሉ አረጋግጠዋል።
በተለይ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ስራ አጥ ምሩቃንን ለማበረታታት ደፍረው ወደ ስራ እንዳይገቡ የሚያደርጉ ማነቆዎችን ለመፍታት የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑ ተነስቷል።
ለአብነትም በብድር አሰጣጥ ረገድ ብድር ለመውሰድ ለ5 አባላት ያስገድድ የነበረው አሰራር ለ4 ወራት የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ ወደ 4 አባላት ዝቅ ማለቱን፣ 10 በመቶ ይጠየቅ የነበረው የቅድመ ቁጠባ በግማሽ መቀነሱ፣ አንድ ሚሊዮን ብር የነበረው የብድር ጣሪያ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የቢዝነስ አማራጭ ሃሳብ ይዘው ለሚቀርቡ ወጣቶች ደግሞ የብድር መጠኑ እስከ 2 ሚሊዮን ብር እንዲለቀቅላቸው ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን ሴቶችን ለማበረታታት ከ18 ዓመት እስከ 34 ዓመት የነበረው የተጠቃሚዎች የእድሜ ጣሪያም እንደ ስራ ፈጠራቸው ታይቶ ከ34 ዓመት በላይ የሆኑ ሊካተቱ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል 3 ወራት እፎይታ ጊዜን ጨምሮ 3 ዓመት የነበረው የብድር መመለሻ ጊዜ ከ4 ወራት የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ ወደ 4 ዓመት ከፍ መደረጉን፣ አንድ በመቶ ይጠየቅ የነበረው የአገልግሎት ክፍያ በመንግስት እንዲሸፈን ወይም ለተጠቃሚዎች ነጻ እንዲሆን መወሰኑ ይፋ ሆኗል።
ወጣቶች እንዲሰማሩባቸው ከተነደፉ የስራ ዕድል አማራጮች መካከል በተመረጡ ወረዳዎች የሚገነቡ 11 ሺህ 900 ዘመናዊ የችርቻሮ ሱቆች፣ 2 ሺህ ዘመናዊ ንግድ ሱቆች፣ 4 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 100 የነዳጅ ማደያዎች፣ 3 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 300 ያገለገሉ መኪናዎችን ተንቀሳቃሽ ዕቃዎች መሸጫ ማድረግ ተጠቅሰዋል።
ከኢንዱስትሪዎች ጋር በተደረገ የቅጥር ስምምነትም 5ሺህ ወጣቶች እንደሚቀጠሩ ተመልክቷል።
በምክክር መድረኩ የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ እንዳለበት ተጠቁሟል።
በቅርብ ጊዜ በየመንገዱ ዳር ሱቆች ተሰርተው የከተማ ገጽታ ያበላሻሉ በሚል እንዲፈርሱ መደረጉ ነዋሪዎችን ያሳዘኑና ተጠቃሚዎችን ለወጪ የዳረገ ተግባር እንደሆነ ተነስቷል።
ወደፊትም ወደተግባር ከመገባቱ በፊት በተጠና አካሄድ መጸፈም እንዳለበትና ባለድርሻ አካላት በተለይም የከተማ ፕላን ኮሚሽን፣ መሬት ልማትና ማናጅመንት፣ ኮንስትራክሽ ቢሮና ፋይናንስ ተቋማት ፈጣን አሰራር በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
የመሰረተ ልማት ግብዓት፣ የኮንትራክሽንና ከተማ ግብርና፣ የሴቶች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ የወጣቶች ምልመላ፣ መታወቂያ የሌላቸው ግን በአዲስ አበባ ለዓመታት የኖሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይና የስራው ጥራት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ ተነስቷል።
ተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ ተጠያቂነት የሚያስከትል ከመዲናዋ ነዋሪዎች የተሰበሰበ የህዝብ ሀብት በመሆኑ በቀሪ አራት ወራት ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካት ተቋማዊ አደረጃጀትን በማጠንከር የወጣቶችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባ ከንቲባው አቅጣጫ ሰጥተዋል።