የአየር መንገዱ አብራሪዎች ከአደጋውም በኋላ በተለመደው ሙያዊ ብቃት ተጓዦችን እያስተናገዱ ነው - ዴኒስ ሙሊንበርግ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር መንገዱ አብራሪዎች ከአደጋውም በኋላ በተለመደው ሙያዊ ብቃት ተጓዦችን እያስተናገዱ ነው - ዴኒስ ሙሊንበርግ
አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአደጋውም በኋላ አብራሪዎች በተለመደው ሙያዊ ብቃታቸው ተጓዦችን ወደ ሚሄዱበት እያደረሱ መሆኑን የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ ገለጹ።
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ንብረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወቃል።
የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች በሙሉ ህይወት አልፏል።
የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በኩባንያው ድረ-ገጽ በኩል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቦይንግ አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በአደጋው ስለሞቱ ዜጎች እና አደጋው በዓለም ዙሪያ በሚኖሩ ዜጎችና የኢንዱስትሪውን ማህበረሰብ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ በጥልቀት ለመረዳት መቻሉን ተናግረዋል።
ከአደጋው በኋላ ባሉት ሳምንታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች በተለመደው ሙያዊ ብቃታቸው ተጓዦችን እያበረሩ መሆናቸውን በግልጽ እንዳሳዩ ነው ዴኒስ ሙሊንበርግ የገለጹት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከአደጋው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት የደረሰው አደጋ ኢትዮጵያንና አየር መንገዱ ከአቪዬሽን ኢንዱስትሪውና ከቦይንግ ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት የማያመላክት እንደሆነ ገልጸው ነበር።
አየር መንገዱ ከባልደረቦቻችን ጋር በመሆን የአየር ጉዞ በሁሉም አየር መንገዶች ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ የሚኮራበት ታሪክ እንዳለውና አየር መንገዱ በኢንዱስትሪው ፈር ቀዳጅና በመሪነት የሚቀመጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ባለው ሰፊ ተደራሽነት የአፍሪካን አህጉር ከዓለም ሁሉም ክፍሎች ጋር እያስተሳሰረና በሚሰጠውም አገልግሎትና የበረራ ደህንነት ከፍተኛ እውቅና የተሰጠው እንደሆነም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አዲስ መንፈስና የአህጉሩ ህዝቦች ኩራትና የለውጥ ወኪል እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ቦይንግ ከአደጋው በኋላ ከኢትዮጵያ የምርመራ ቡድን ጋር በመሆን ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ጓደኞችና ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ የተሰማውን ሀዘን እየገለጸና እያጽናና መቆየቱን ዴኒስ ሙሊንበርግ ጠቁመዋል።
በበረራ ደህንነት ባለን የጋራ እሴት የቦይንግ ኩንባያ ያለውን ሁሉም አቅም በመጠቀም በአደጋው ምን እንደተፈጠረና በተቻለው ሁሉ አቅም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደህንነቱ የተጠበቀ የአየር በረራ ስርአት ለመገንባት ስኬታማ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት በማድነቅ ምስጋና እንደሚገባው አመልክተዋል።
የቦይንግ ኩባንያ ከሁሉም ደንበኞቹና አጋሮቹ ጋር በመሆን ተጓዦች በኩባንያው እምነትና መተማመን እንዲኖራቸው የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቦይንግ በሚሰራው ስራ ደህንነት፣ የላቀ ብቃትና ሙያዊ ስነ ምግባር በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ስራ እንደሆነና ይህ ጉዳይ አሁን የዘርፉ ኢንዱስትሪ የሚጠይቀው እንደሆነም አክለዋል።