የኢሶህዴፓ አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በመጪው ሰኞ እንደሚጀመር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሶህዴፓ አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በመጪው ሰኞ እንደሚጀመር ተገለጸ
ጅግጅጋ መጋቢት 19/2011 የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ እንደሚያካሄድ የፓርቲው ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንጅነር መሐመድ ሻሌ ኢሳቅ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባኤው በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ይደነግጋል ።
በዚህም ድርጅታዊ ጉባኤው ሰባት መቶ ድምፅ ያላቸው የፓርቲ አባላትን ጨምሮ ከ2ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ከመጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል።
ጉባኤው የፓርቲ አመራርና አባላት የሀሳብ እና የተግባር እንድነት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል።
ከአሁን ቀደም በድርጅቱ በተካሄዱ የተናጠል ውይይቶች በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም ላይ የማሻሻያ ሃሳቦች መነሳታቸውን አስታውሰዋል።
የማሻሻያ ሃሳቦች በጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጸድቁ አመልክተው በርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራር እስከ አባል ድረስ ውይይት ተደርጎባቸው ለጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርቡ ሰነዶች ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ውስጥ ያከናወናቸው ስራዎች በሰነድ መልክ ተዘጋጅቶ በጉባኤው ለውይይት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
ጉባኤው በመልካም አስተዳደር፣በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ክልላዊና ሀገራዊ ለውጥ ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ኢሶህዴፓ ከነችግሮቹም ቢሆን ለሁለት አስርት ዓመታት ክልሉን መምራቱን ያስታወሱት ኢንጅነር መሐመድ የክልሉ ህዝብ ከደርጅቱ ጎን በመሆን የክልሉን ልማትና ሰላም እንዲያስቀጥልም አመልክተዋል።