የኦዴፓን ምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ባዛርና አውደ ርዕይ በጅማ ተከፈተ

87

ጅማ መጋቢት 19/2011 የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ /ኦዴፓ/ የተመሰረተበት 29ኛው ዓመት በዓል  ምክንያት በማድረግ ሞዴል የጥቃቅንና አንስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማህበራት የተሳተፉበት ባዛርና አውደ ርዕይ ዛሬ በጅማ ከተማ ተከፈተ፡፡

ለሶስት ቀናት የሚቆየው ባዛርና አውደ ርዕዩ የተከፈተው የከተማዋ  አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ አባገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ተመርቆ ነው፡፡

በዝግጅቱ ከተሳተፉት ሞዴል ኢንተርፕራይዝ ማህበራት ተወካዮች መካከል ወጣት ካሳሁን ተስፋዬ እንዳለው ባዛርና አውደ ርዕዩ  የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡

" ቅራጻ ቅርጽና የከረቡላ መጫወቻ ይዘን ቀርበናል " ያለው ወጣት ካሳሁን በተለይ በአብዛኛው ከአዲስ አበባ የሚመጣው የከረቡላ መጫወቻ ለመተካት በጥራት እንደሚሰሩ ለማስተዋወቅ ዝግጅቱ እንደሚጥቅማቸው ተናግሯል፡፡

ወጣት ኑሩ ሺፋ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት  በአብዛኛው ወጣት ከልማት ይልቅ ለፖለቲካ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጥ  ገልጿል፡፡

ኦዴፓ የተመሰረተበት የ29ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በጅማ ከተማ የተዘጋጀው ባዛርና አውደ ርዕይ  ወጣቱ ለልማት እንቅስቃሴ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥና ለዚህ መነሳሳት እንደሚፈጥር ተናግራል፡፡

" እኔም ከተፈጠረው መነሳሳት ተጠቃሚ በመሆን ከድህነት ለመውጣት እሰራለሁ" ብሏል፡፡

የጅማ ከተማ አስተዳደር የወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር  ወጣት  አብዶ አቂብ  የድርጅቱን የምስረታ በዓል  ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ባዛርና አውደ ርዕይ  ወጣቶች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚያግዝ መሆኑን  ገልጿል፡፡

ከዚህ ዝግጅት በተጓዳኝ በሚካሄደው ውይይት  ወጣቶች የልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበት የሃሳብ ልውውጥ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ጋር እንደሚደረግም አመልክቷል፡፡ በዝግጅቱ  የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች፣ ዘመናዊና የባህል አልባሳት፣ የጽዳትና የውበት እንዲሁም የግብርና ምርቶች ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም