ቀጥታ፡

የባዮፊውል ልማት አጠቃቀምና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

አዳማ መጋቢት 19/2011 የባዮፊውል ልማት አጠቃቀምና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የሚያስችል ግብዓት ለማሰባሰብ የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኩዋንግ  ቱት ፋሞ በወቅቱ እንደገለፁት ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት ያስፈለገው አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ከብክለት የፀዳ የባዮፊውል ልማት ለማከናወን ነው።

ከእፅዋትና አትክልት ታዳሽ ኃይል በማምረት ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት የረቂቅ አዋጁ አላማ እንደሆነ ተናግረዋል ።

ሀገሪቱ ከውጭ እያስገባች ላለችው ነዳጅ ግዥ በየዓመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እያወጣች መሆኗን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ከታዳሽ ኃይል ልማት የሚገኘውን ተረፈ ምርት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ለማዋል እንደሚያስችል ተናግረዋል ።

ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠርና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነም አመላክተዋል ።

ከስኳር ተረፈ ምርት ኢታኖል በማምረት በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን 55ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማዳን መቻሉን በተሞክሮነት ጠቅሰዋል።

ባዮፈውል ለማልማት፣ለማስፋፋትና ለመጠቀም የሚያስችል ሕግ አገሪቷ  እንዳልነበራትም ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።

አዋጁ ዘላቂ የዘርፉን ልማት ለማከናወን ፣ ለመጠቀምና ለማስተዳደር አዲስ አሰራር ለመዘርጋት የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴሩ የባዮ ፊውል ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ገሰሰ ናቸው።

በሀገር ውስጥ የሚመረት ታዳሸና ከብክለት ነፃ የሆነ የሀይል ምንጭ እንዲኖረን ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

"የልማት የማምረት የሙያ ብቃት አገልግሎት ፣ የግብአት አቅርቦትና የማምረቻ  መሳሪያዎች  ጭምር በሕግ ይወሰናሉ" ያሉት ደግሞ የሚኒስትሩ የሕግ ባለሙያ አቶ አለማየሁ ማንደፍሮ ናቸው።

ዘርፉ በመንግስትና በግል ሴክተር ለማልማት እስትራቴጂ መቀረፁን ገልጸው "በሂደት የመንግስትን ሚና በመቀነስ ልማቱ በግሉ ዘርፍ እንዲመራ ይደረጋል" ብለዋል ።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም